ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሣምንት የሚዘጉት ተማሪዎች የቤተሰቦቻቸውን እና የዘማቾች ሰብል ስብሰባ እንዲያግዙ ነው

70

አዲስ አበባ፣  ህዳር 25/2014 (ኢዜአ) አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በተለመደ የፈጠራ ዘገባቸው መንግስት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ተማሪዎችን ለጦርነት ማቀጣጠያነት ሊጠቀም ነው በማለት የሚያናፍሱት ወሬ ሐሰተኛ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሣ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተማሪዎች ሰብል በመሰብሰብ እንዲያግዙ ትምህርት ሚኒስቴር ለአንድ ሣምንት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መዝጋቱን ገልጸዋል።

ይህ በቀደሙት ጊዜያትም ሲደረግ የቆየ መሆኑንና በዚህ ዓመትም ተማሪዎች በማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሣተፉ መደረጉ ከኢትዮጵያዊነት ባህል የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ይህንን የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል ለማዳበር የተደረገውን በጎ ተግባር በአሉታዊ መልኩ እየዘገቡት መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን "መንግስት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ተማሪዎችን ለጦርነት ማቀጣጠያነት ሊጠቀም ነው" በሚል የዘገቡት ፍጹም ሐሰተኛና የኢትዮጵያዊነት ባህልን ካለማወቅ የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከኅዳር 27 እስከ ታኅሣሥ 3 ቀን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚዘጉና ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ያልተሰበሰቡ የዘማቾች ሰብል መሰብሰብና ቤተሰቦቻቸውን የመርዳት ዘመቻዎች እንደሚካሄዱ መግለጹ ይታወቃል።

በሌላ ዜና ሚኒስትር ዴኤታዋ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው በመምጣት የአገራቸውን እውነታ እና ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ለማስረዳት የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬት በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም