የመንግስት ሠራተኞች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ

170

ባህር ዳር ህዳር 24/2014 (ኢዜአ)”ልጆቻችን አሸባሪውን ህወሓት ለመፋለም ወደግንባር ቢዘምቱም የመንግስት ሠራተኞች የደረሰ ሰብላችንን በመሰብሰባቸው ኮርተናል” ሲሉ የዘማች ቤተሰቦች ተናገሩ።

የመንግስት ሠራተኞች ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረብ ቀበሌ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰብስበዋል።

ሰብላቸው ከተሰበሰበላቸው የዘማች ቤተሰቦች መካከል ወይዘሮ የምክር አንዳርጌ እንዳሉት፣ ሁለት ልጆቻቸው መንግስት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው ጠላትን በግንባር እየተፋለሙ ይገኛሉ።

“እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ጉልበት ስለሌለን ሰብላችንን ለመሰብሰብ ጨንቆን ነበር” ያሉት ወይዘሮ የምክር፣ “የመንግስት ሠራተኞች የበቆሎና የዳጉሳ ሰብላችንን ስለሰበሰቡልን ኩራት ተሰምቶናል” ብለዋል።

ልጆቻቸው ሀገርና ህዝብን ከአሸባሪውና ወራሪው ህወሓት ነፃ ለማውጣት ወደግንባር በመሄዳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ በድልና በሰላም እንደሚመለሱም ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ልጃቸውን መርቀው ወደግንባር እንደሸኙ የገለጹት ሌላዋ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቻላቸው አዲሱም የበቆሎ ሰብላቸው በሠራተኞች እንደተሰበሰበላቸው ተናግረዋል።  

“ሰብሌ መሰብሰቡ ልጄ ለእኛ መጨነቁን ትቶ ጠላትን በአንድ ልብ ይፋለማል” ያሉት አርሶ አደሩ፣ ድጋፉ ለሌሎችም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

”ኢትዮጵያን ለመበተን ቆርጦ ከተነሳው የአሸባሪ ቡድን ጋር ወንድሞቻችን በጀግንነት እየተዋደቁ ይገኛሉ” ያሉት ደግሞ በሰብል ስብሰባ ስራው የተሳተፉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባልደረባ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው።

“እነሱ ከጠላት ጋር ሲዋደቁ እኛ ደግሞ የኋላ ደጀን ሆነን የደረሱ ሰብሎችን እንሰበስባለን፤ ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብና ማገዝ የሁላችንም ግዴታ ነው” ብለዋል።

“የህልውና ዘመቻው በድል እንዲቋጭ የዘማች ቤተሰቦችን መንከባከብ ያስፈልጋል” ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ናቸው።

“የዘማች ቤተሰቦች ሰብል ሳይባክን በወቅቱ መሰብሰብ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው” ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው 16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል ምክንያት በማድረግ ከህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የዘማች ቤተሰቦች ሰብል እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

“እንደ ጀግኖች አባቶቻችን የራሳችንን ታሪክ በመስራት ሀገር ለመበተን የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በመመከት ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን” ብለዋል።

አሸባሪውን ቡድን እየተፋለሙ የሚገኙ ዘማች ቤተሰቦችን ሰብል መሰብሰብ፣ ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብና መደገፍ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከገባበት ዋሻ እንዳይወጣ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ተከታትሎ ባለበት ሊያስቀረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሰብል ስብሰባው ላይ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የሥራ ፈጠራና ስልጠና፣ የቱሪዝም፣ የትምህርት ቢሮ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተቋማት ሠራተኞች ተሳተፈዋል።