አሸባሪው በንጹሃን ዜጎችና በእምነት ተቋማት ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዝ ተጠየቀ

75

ሠመራ ፤ ህዳር 24/2014(ኢዜአ)... አሸባሪው ህወሃት በንጹሃን ዜጎችና የእምነት ተቋማት ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ተጠየቀ።

የአፋር ክልል ጠቅላይ ሼሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ ደርሳ አሸባሪው ህወሓት በእብሪት በወረራቸው አካባቢዎች የፈጸማቸውን አስነዋሪ ድርጊቶች አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤አሸባሪው ቡድን በየደረሰባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎችን በግፍ ከመጨፍጨፍና ከቀዬያቸው ከማፈናቀሉም ባሻገር ሀብትና ንብረት ዘርፏል፤  አውድሟል።


የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአፋር ክልል አካባቢዎች ከ12 በላይ መስጂዶችን በከባድ መሳሪያዎች ደብድቦ ጉዳት አድርሷል።

በዚህም ቅዱስ ቁርአንን ጨምሮ የተለያዩ የእምነት ማስተማሪያ መጽሐትን በማቃጠልና በመቅደድ ማውደሙንም ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።


በክልሉ በሽብር ቡድኑ ጥቃት ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል አደአር፣ ተላላክ፣ ሀደለኤለ ፣ ጭፍራ፣ ራህሌና መጋሌ ወረዳዎች ይገኙበታል።


ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው እንዳስረዱት፤ አሸባሪው ቡድን ባይሳካለትም ቅሉ በንጹሃን ዜጎችና የእምነት ተቋማቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያውያን ወደ ሃይማኖት  ግጭት ለማስገባት ያለመ  ነው።

ህዝቡ የጥፋት ቡድኑን እኩይ ሴራ ተገንዝቦ  ያለመውን የመከፋፈል ወጥመድ በብልጠት በማለፍ ጠላቱን በአንድነትና በፅናት እየመከተ አመርቂ ድል እያስመዘገበ ይገኛልም ብለዋል።


የሽብር ቡድኑ የፈጸመው በየትኛውም ምድራዊ ህግም ሆነ የእምነት ቀኖና ተቀባይነት የሌለውና ሊወገዝ የሚገባው አሳፋሪ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።


ስለሆነም የሽብር ቡድኑ በእብሪት በወረራቸው አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎችና እምነት ተቋማት ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃትና የሽብር ተግባር  የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውግዘው ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም