የወንጪ ሐይቅ የዓለም አቀፍ ተመራጭ የቱሪዝም መንደር መሆን ማኅበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማትን ያበረታታል

206

አዲስ አበባ ፣ህዳር 24/2014(ኢዜአ) የወንጪ ሐይቅ ዓለም አቀፍ ተመራጭ የቱሪዝም መንደር ተብሎ መሸለሙ ለሌሎች ማኅበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት እንቅስቃሴ ብርታት የሚሰጥ ነው ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

ከአዲስ አበባ 135 ኪሎ ሜትር ርቀት ከወሊሶ-አምቦ ጎዳና መሃል ላይ በእሳተ ጎመራ የተፈጠረው ወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ገባውን በድንቅ አረንጓዴያማ ጋራዎች የተከበበ ለዓይን የሚያጓጓ ማራኪ ስፍራ ነው።

በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተተከለውን ታሪካዊና ጥንታዊውን ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ያቀፈው ዝምተኛው ወንጪ ሐይቅ ከእምቅ የብዝሃ ሕይወት ባለቤትነቱ ባሻገር ለአካባቢው ነዋሪዎች ለመጠጥነት ይውላል።

ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ታዲያ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሽልማትን አሸንፏል።

ሽልማቱ ትናንት በስፔይን ማድሪድ ከተማ በተካሄደው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት 24ኛ ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ በይፋ የተሰጠ ሲሆን የሽልማቱ ማብሰሪያ መርሃ ግብርም በወንጪ ሐይቅ ተከናውኗል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ እንዳሉት ባህላዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን የታደለው ወንጪ ሐይቅ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር መሰኘቱ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማትና ተጠቃሚነት ፋይዳው ጉልህ ነው።

ሽልማቱ ለሌሎች ማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ልማት እንቅስቃሴዎች ተምሳሌትና ብርታት እንደሚሆን ገልጸው፤ እንደ አገርም መንግስት በቱሪዝም ልማት ረገድ ትክክለኛ መንገድ ላይ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

ወንጪና አካባቢው ለዚህ ሸልማት እንዲበቃ የአካባቢው ማኅበረሰብ አካባቢውን በመጠበቅ ሚናው የማይተካ እንደነበረም ገልጸዋል።

ቱሪዝም ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ 10 ቁልፍ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር ዋና ትኩረቱ ዓይነተ ብዙ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና ማስተዋወቅ ከዘርፉ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ቱሪዝም በተለይም ለታዳጊ አገራት ከድህነት ለመውጣት አንዱ ቁልፍ አማራጭ በመሆኑ ማኅበረሰብን ተጠቃሚ በሚያደርግ ቱሪዝም ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የወንጪን ስነ ምህዳር ጠብቆ እንዳቆየ ሁሉ ወደፊትም የአካባቢ ጥበቃና እንግዳ ተቀባይነት ባህሉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታዬ ጉዲሳ ወንጪን ባለፈው አንድ ዓመት ከ46 ሺህ በላይ ሕዝብ ስለመጎብኘቱና ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በገበታ ለሀገር የሚገነባው ወንጪ ደንዲ ፕሮጀከት እውን ሲሆን ደግሞ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የዞኑ ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታም 4 ሺህ ቋሚና 7 ሺህ ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ገልፀው፤ ከወዲሁ 87 የስራ አይነቶች ተለይተዋል ብለዋል።

በአካባቢው ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት የሚሆኑ ይዞታዎችን የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ባለሀብቶች በወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ይታየው ታሪኩ በበኩላቸው ወንጪ የተመድ ዓለም አቀፍ ተመራጭ የቱሪዝም መንደር አሸናፊ ሆኖ መመረጡ እንደ አገር ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር መዝገብ መስፈሩ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምርና ከወንጪም ባለፈ ለሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችም የመጎብኘት አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህም ለማኅብረሰቡ እና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለ ድርሻ አካላት ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም