ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው "ሮያል ሶሳይቲ" የተሰኘው ማህበር ቀዳሚው አፍሪካዊ አባል ሆኑ

162
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 ኢትዮጵያዊው የስነ-እፅዋት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በዓለም ስመ-ጥር የሆኑ ተመራማሪዎችን የሚያሰባስበውና "ሮያል ሶሳይቲ" የተሰኘው ማህበር ቀዳሚው አፍሪካዊ የውጭ አባል ሆነው ተመርጠዋል። ሮያል ሶሳይቲ አንድ አፍሪካዊን በዚህ ደረጃ አባል ሲያደርግ በ360 ዓመት ታሪኩ ፕሮፌሰር ሰብስቤ የመጀመሪያው ናቸው። ፕሮፌሰሩ "ደስታውን እንደራሴ ሳይሆን እንደ አገር የኢትዮጵያ ህዝብ ደስታ ነው የማየው" ይላሉ። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1978 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕይወት ትምህርት ክፍል ረዳት ምሩቅ ሆነው በወቅቱ የሳይንስ ፋካሊቲ ዲን በነበሩት በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ነበር የተቀጠሩት። ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው አገልግሎታቸው 40 ዓመታትን የደፈኑት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ በቅርቡ ከታዋቂው የእንግሊዙ የሳይንቲስቶች ማኅበር/ሮያል ሶሳይቲ/ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የማኅበሩ ባልደረባ ሆነው ተመርጠዋል። በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1982 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ፣ በ1985 ከስዊድኑ አፕሳላ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት የሳይንስ ምሁሩ፤ በሥነ ዕጽዋት ምርምር የተቀላቀሉት ገና በማለዳው ዩኒቨርሲቲውን በተቀላቀሉ በሁለተኛው ዓመት ነበር። በስዊዲኑ አፕሳላ ዩኒቨርሲቲና በወቅቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ትብብር በ1980 በተጀመረው 'የኢትዮጵያ ዕጽዋት ጥናት ፕሮጀክት' በመጀመሪያ በረዳት ተመራማሪነት፤ በኋላም በሙሉ ተመራማሪነት አገልግለዋል። በመጨረሻም 30 ዓመታት የፈጀውን ይህንኑ ፕሮጀክት ለ16 ዓመታት መርተዋል። በ10 ተከታታይ ዳጎስ ያሉ ጥራዞች ካወጣው 'የኢትዮጵያ ዕጽዋት ጥናት ፕሮጀክት' በተጨማሪም ከኖርዌይ-ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሬት ተክል የጥናት ፕሮጀክት በመቅረጽ፤ በግላቸው አምስት፤ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ደግሞ 11 የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመርቀዋል። ፕሮፌሰር ሰብስቤ በግላቸው ከአምስት በላይ ዳጎስ ያሉ የምርምር መጽሐፍትን፤ እንዲሁም ከ140 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በታዋቂ ዓለም አቀፍ የጥናት መጽሃፍት አሳትመዋል። ከ50 በላይ የሁለተኛ ዲግሪ፣ በአሁኑ ወቅት ያልጨረሱትን ጨምሮ 30 የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎቻቸውንም አማክረው አስመርቀዋል። በዕፅዋት ብዝሃ ሕይወት፣ በዕጽዋት ሥነ-ምህዳር፣ ቤተሰብ፣ ዝርያና ስርጭት ላይ ምርምራቸውን የሚያጠነጥነው ሳንቲስቱ፤ በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ የአፍሪካ አገሮች ባደረጉት ጥናት ከ50 በላይ አዳዲስ የዕጽዋት ቤተሰቦችን በመለየት ሳይንሳዊ ስያሜ ሰጥተዋል። ከዚህም ባለፈ በእርሳቸው ስም አዲስ የዕጽዋት ዝርያ ተሰይሞላቸዋል። በፕሮፌሰር ሰብስቤ ዕይታ ግን 'ሌላ ለሰው በስም ከሚሰይምልህ አንተ በየአገራቱ ወጥተው ወርደህ አዳዲስ ስያሜ የሰጠኸው ስራ የላቀ ነው"ይላሉ። ድንበር ተሻጋሪ ጥናትና ምርምራቸው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ዕውቅና እንደፈጠረላቸው የሚናገሩት ሳይንቲስቱ  በ2016 በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ሥራን ላከናወነና ከእንግሊዙ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ጋር ተግባራዊ ስራ ለሰሩ ሳይንቲስቶች የሚሰጠውን የኬው ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸለሚ ነበሩ። ሽልማቱም የኢትዮጵያን ብዝኃ ሕይወትን ለረዥም ጊዜ በማጥናትና በመመርመር ኅብረተሰቡም ሆነ አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዓለምም እንዲታወቅ ባደረጉት አበርክቶት ነበር። በቅርቡ አባል የሆኑበት የሮያል ሶሳይቲ 'እንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይኖራት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው ተቋም ነው' የሚሉት ፕሮፈሰር ሰብስቤ፤ ተቋሙ ከእንግሊዝና ለጋራ ብልፅግና /ኮመን ዌልዝ/ አባል አገሮች ውጭ አባል ማድረግ መጀመሩን ይገልጻሉ። ያም ሆኖ በብዛት ከአውሮፓና አሜሪካ የሚመረጡ የውጭ ዓለም አቀፍ የምህንስና፣ የፊዚክስ፣ የፈጠራና በዕፅዋት ሳይንስ ሳይንቲስቶች እንደነበር ገልጸው፤ ወሰን ተሻጋሪ የምርምር ስራቸውና ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር ያከናወኑት ውጤታማ ስራ ለዚህ እንዳበቃቸው ይናገራሉ። ሳይንቲስቱ "እነ አይዛክ ኒውተንና ቻርለስ ዳርዊን መሰል ታላላቅ ሳይንቲስቶች አባል በነበሩበት ማኅበር፤ ለአባልነት መመረጥና ከታላላቅ ሰዎች ተርታ ስምህን መዝገብና ፈርም ስትባል የሚፈጥረው ደስታ ከፍ ያለ ነው" ይላሉ። ያም ሆኖ 'ዕውቅናው በግል የተደረገ ሳይሆን እንደ አገር ነው የማየው" በማለት ደስታው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር ነው ብለዋል። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሚያደርጉት ምርምር በተጨማሪ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅን በዲንነት ከመምራት ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። በአሁኑ ውቅትም የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም