ብሄር ብሄረሰቦች አንድነታቸውን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ክብር ዘብ ሊቆሙ ይገባል

120

አሶሳ ህዳር 24 / 2014 -(ኢዜአ ) ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት እሴታቸውን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ክብርና ታላቅነት ዘብ ሊቆሙ ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ አስገነዘቡ ።

16ኛው የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልና የመቻቻል ቀን ዛሬ በአሶሳ ከተማ በጣምራ ተከብሯል፡፡

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የበርካታ ብሄረሰቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያን ዳግም ታላቅነቷን ማረጋገጥና ለክብሯ ዘብ መቆም ከልጆቿ ይጠበቃል፡፡

ብሄር ብሄረሰቦች የመቻቻልና የአብሮነት እሴታቸውን በማጠናከር የኢትጵያን ህልውናና ሉአላዊነት ሊያስከብሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"እኛ ካልመራን ሃገር ትፍረስ ብለው የተነሱ ህወሀትና የጥፋት መልዕክተኞቹ እየፈጸሙብን የሚገኘው ውስብስብ ችግር ታሪክ ይቅር የማይለው ነው" ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከጅምሩ አንስቶ በውስጥና በውጪ ጠላቶች እንቅፋት ቢበዛበትም ብሔር ብሔረሰቦች ሴራውን ተባብረው በማክሸፍ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ሆነው ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ሀይሎችን  ሴራ ከማምከን ጎን ለጎን በግንባር እየተፋለመ ላለው ጀግናው መከላከያ ሠራዊት ድጋፉቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት መስኪያ አብደላ በበኩላቸው "ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን ጠብቀን የቀጠልነው በብሔረሰቦች መካከል ባለው ጠንካራ የመቻቻል ባህል ጭምር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ሽብርተኛው ህወሃት ሀገር የማፍረስ ሴራውን ለማሳካት በንጹሃን ላይ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ መሆኑን ጠቁመው የአሸባሪውን የጥፋት ተልእኮ ለመግታት እየተፋለመ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

ብሄር ብሄራቦችና ህዝቦች በህልውናቸው ላይ የተነሳን ጠላት በጋራ በመታገል የሀገራቸውን ክብር ፣ ሰላምና የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሸባሪውን ወራሪ ሀይል ለመፋለም በግንባር ተገኝተው ጦርነቱን መምራታቸውን በማድነቅ  የህልውና ትግሉ በአጭር ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ የበአሉ ተሳታፊ  አቶ እንድሪስ መሃመድ ናቸው።

ወይዘሮ ከልቱም ባበክር በበኩላቸው ሽብርተኛው ህወሃት በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ስም የግል ጥቅሙን ሲያስፈጽም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪው ከስልጣን ከተወገደም በኋላም  በብሄረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ሃገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ሲጥር እንደነበር ጠቁመው "አሸባሪው በአሁኑ ወቅት በብሔር ብሄረሰቦች የተባበረ ክንድ እየተመታ መፈናፈኛ አጥቷል" ብለዋል፡፡

የሽብርተኛው ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ።

የበዓሉ ተሳታፊዎች አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት “በቃ” በሚል አውግዘዋል፡፡

“ወንድማማችነት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ የብሄረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም