ከዳያስፖራው በአንድ ወር 3 ሚሊዮን ዶላር ለተጎጂዎች ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል

51

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2014 (ኢዜአ) ከዳያስፖራው በአንድ ወር 3 ሚሊዮን ዶላር ለተጎጂዎች ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል።

"አይዞን ኢትዮጵያ" የተሰኘ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘደ ጥቅም ላይ ከዋለ ጀምሮ ዳያስፖራዎች በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዳያስፖራዎች የሚያደርጉት ድጋፍ እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል።

ይህንኑ በማስመልከት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ እንዳሉት በአንድ ወር ጊዜ ብቻ ከ15 ሺህ ዳያስፖራዎች 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል።

የገንዘብ ማስተላለፊያ አማራጩ በተለይም በዳያስፖራ በተደጋጋሚ ይቀርብ የነበረውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ጥያቄ የመለሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገንዘብ ማስተላለፊያ ፕላትፎርሙ አለም አቀፍ የክፍያ መስመር ማመቻቸቱን ገልጸው አማራጩ በተለይም በዳያስፖራው በተደጋጋሚ ይቀርብ የነበረውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል፡፡

የክፍያ ስርዓቱ ያለምንም ተቆራጭ ገንዘብ ድጋፉ በቀጥታ አገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው "የአይዞን ኢትዮጵያ" የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕላትፎርሙ ውጤታማ እንዲሆን አለም አቀፍ የክፍያ መስመሩን አመቻችቷል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ በርካታ ዜጎች በችግር ውስጥ እንዳሉ የገለጹት ደግሞ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም