የ#NoMore ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ በጀርመን ከተሞች ይካሄዳል

59

ህዳር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ’በቃ’ ወይም #NoMore ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ይካሄዳል::

ሰልፉ በበርሊን፣ ቦን እና ፍራንክፈርት ከተሞች በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ እንደሚካሄድ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዘላለም ደበበ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የፍራንክፈርቱ ሰልፍ መነሻውን ከሃውፕትፍሬድሆፍ አደባባይ በመነሳት መዳረሻውን በከተማው በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በማድረግ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።በሰልፉ ላይ ከዶርትሙንድ፣ ሙኒክ፣ ስቱትጋርት፣ ላይፕዚግና በሌሎች የጀርመን ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

በፍራንክፈርት በሚካሄደው ሰልፍ ላይ በሶሪያ ባለው ጦርነት ተፈናቅለው በጀርመን አገር የሚኖሩ ሶሪያውያን እንደሚሳተፉና በምዕራባውያን ሴራ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገደችው አገራችን ተማሩ ጣልቃ ገብነት እንዳትፈቅዱ የሚሉ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉም ነው አቶ ዘላለም የገለጹት።

የበርሊኑ ሰልፍ በጀርመን መራሒተ-መንግስት መስሪያ ቤት (Federal Chancellery) ፊት ለፊት የሚካሄድ ሲሆን፤ ሰልፈኞቹ ጀርመንን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ጥሪ ያቀርባሉ ብለዋል።

በቦን የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማው ዋና መቀመጫውን ያደረገው የጀርመኑ ዶይቸ ቬለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጣቸውና አድሏዊና የተሳሳቱ ዘገባዎች ማስተካከል እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል።

በሶስቱ የጀርመን ከተሞች የሚካሄዱት ሰልፎች ላይ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ፣ ኤርትራውያን፣ የአፍሪካ አገራት ዜጎችና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፋሉ ነው ያሉት አቶ ዘላለም።

በጀርመን የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ንግግር እንደሚያደርጉ አክለዋል።የበቃ ወይም #NoMore ዘመቻ ሰላማዊ ሰልፎች ነገ በፈረንሳይ ፓሪስ እንዲሁም ከነገ በስቲያ በሊባኖስ ቤይሩትና በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ከተሞች ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም