የአገራችንን ሕልውና እያስጠበቅን ልማታችንን እናፋጥናለን

85

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2014 (ኢዜአ) የአገራችንን ሕልውና እያስጠበቅን ልማታችንን እናፋጥናለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሣ ገለፁ።

አቶ ሺመልስ በወሊሶ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሲያስጀምሩ 'የለውጡ መንግስት የማይጨርሰውን ፕሮጀክት አይጀምርም' ሲሉ ተናግረዋል።የወሊሶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

አገር ለማፍረስ የተነሱትን አሸባሪዎቹን ህወሓት እና ሸኔን እያጠፋን ልማታችንን እናፋጥናለን ብለዋል።አቶ ሺመልስ ሕዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ አካባቢውን በመጠበቅና ለመከላከያና ለጸጥታ አካላት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።አሁን እየተገኘ ያለው ድል በሕዝቡ አንድነትና ትብብር በመሆኑ የመጨረሻው ድል እስከሚገኝ ድረስ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

አሸባሪዎቹን በቶሎ አጥፍተን በሙሉ አቅማችን ወደ ልማት እንቅስቃሴያችን የምንመለስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲሉም አክለዋል።የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ግንባታው የተጀመረው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለበት ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ ጠቁመዋል።ግንባታው በ230 ሚሊዮን ብር እንደሚከወን ተገልጿል።የወሊሶ ከተማ የመጠጥ ውሃ ሽፋን 61 በመቶ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት በ1 ዓመት ከ6 ወር ሲጠናቀቅ ሽፋኑን ከመቶ ፕርሰንት በላይ ያደርሰዋል ተብሏል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ የዓመታት ጥያቄያቸውን የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል።የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር የሚያደርጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም