ኮርፖሬሽኑ ለአገር ውስጥ አምራቾች የንግድ ትስስር ለመፍጠር እየሰራ ነው

59
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ የውጭ አገራት አምራቾችን ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር በንግድ ለማስተሳሰር እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የንግድ ለንግድ ትስስርና የምክክር መርሐ-ግብር የተመረጡ ስድስት አምራቾች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ለሊሴ ነሚ በሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የአምራቾቹን የግብአት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ኮርፖሬሽኑ ከ40 እስከ እስከ 60 በመቶ በአገር ውስጥ አምራቾች በኩል ድጋፍ ያደርጋል። የተመረጡት የአገር ውስጥ አምራቾች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚገኙ አምራቾች ግብአት ለማቅረብ አቅም እንዳላቸው ኮርፖሬሽኑ ማረጋገጡን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ላሉ አምራቾች ግብአት እንዲያቀርቡ የንግድ ትስስር የተፈጠረላቸው ስድስት የአገር ውስጥ አምራቾች ሲሆኑ በቀጣይ ከሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ተመሳሳይ ትስስር እንደሚፈጠር አስታውቀዋል። የንግድ ለንግድ ትስስር ፈንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ወዳጆ በበኩላቸው የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማሳደግ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር የሚደረገው የንግድ ትስስር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በመጀመሪያው ዙር ለሰባት አምራቾች ተመሳሳይ የንግድ ትስስር ድጋፍ መደረጉን የጠቀሱት አቶ እውነቱ በቀጣይ ለሦስት የአገር ውስጥ አምራቾች ድጋፍ ለማድረግ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም