በኢትዮጵያዊ ማንነት ድል ጨብጦ የሚሄደውን ሠራዊት ማንም ሊያስቆመው አይችልም

85

ህዳር 24/2014/ኢዜአ/በኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት "ከዚህ በኋላ ማንም፣ በምንም ሊያስቆመው አይችልም፤ ምክንያቱም ድል ጨብጦ የሚሔድ ሆኗል" ይላሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ።

ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ በጋሸና፣ በሚሌ፣ በላሊበላና በሌሎችም አካባቢዎች በሠራዊቱ የተገኙት ድሎች መሰረታዊና የመጨረሻውን ድል የሚያመላክቱ ናቸው ሲሉም ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በግንባር ከሠራዊቱ ጋር መሰለፋቸው ከምንም በላይ አገር ማስቀደማቸውን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገር ከስልጣን፣ ከወንበርና ከክብር ሁሉ በላይ ናት በማለት ወደ ግንባር መዝመት ለመላው ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ወኔን ያላበሰ ነው ብለዋል።

በጋሸና፣ በሚሌና በላሊበላ የተገኙት ድሎች መሰረታዊና የመጨረሻውን ድል የሚያመላክቱ ናቸው ያሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ በዋናነት ጋሸና በወታደራዊ ስትራጄክ እይታ ጉልህ ስፍራ አላት ብለዋል።

ይህ መሆኑም ጠላት ሽንፈቱን እንዲከናነብና ብትንትኑ እንዲወጣ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ስፍራው በወገን ጦር ቁጥጥር ስር መዋሉ የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ እንዲበታተንና የሞራል ድቀት እንዲደርስበት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

ጠላት ከደረሰበት ሽንፈት ዳግመኛ እንዳያንሰራራ፤ የወገን ጦር ድል እንዲስፋፋና ቀጣይነት እንዲኖረው ያደረገም ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ሲሄዱ አገር ሄዳለች፣ ሕዝብ ሄዷል ያሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ዕእነዚህ ሁሉ የድል ሃይል ናቸው ብለዋል።

በዚህ ሁኔታ የመከላከያ ሠራዊቱ ያካበተው ልምድ፣ እውቀትና ጀግንነት ከዚህ በኋላ ማንም ሊያስቆመው በማይችልበት ሁኔታ አጠንክሮታል ብለዋል።

የህወሓት የሸብር ቡድን የአገር ክሕደት ወንጀል ሲፈጽም የመጀመሪያው አይደለም ያሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ በካራማራ ጦርነትም ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ኢትዮጵያን መውጋቱን አስታውሰዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር አባላት ግንባር በመዝመት፣ ሠራዊቱን በማሰልጠንና ልምዳቸውን በማካፈል ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም