ማእከሉ ለዘማች ቤተሰቦች 600 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

71

ባህር ዳር ህዳር 23/2014 ኢዜአ) "ግሬስ የልጆችና ቤተሰቦቻቸው ማዕከል" በባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች 600 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።

የማዕከሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ አሳብ ዛሬ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት የዘማች ቤተሰቦችን መደገፍና መንከባከብ የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባል።

ማዕከሉ በባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች 600 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍ 93 ኩንታል ጤፍ፣ 1ሺህ ሊትር የምግብ ዘይትና ስምንት ኩንታል ሽሮ ያካተተ መሆኑን  ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ማዕከሉ በህልውና ዘመቻው ወደ ግንባር የዘመቱ የሚሊሻና የተመላሽ ሠራዊት ቤተሰቦችን ለመደገፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ የሺሀረግ ፈንታሁን በበኩላቸው ህብረተሰቡ የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

ማእከሉ ያደረገው ድጋፍ  252 የዘማች ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል ።

ከእዚህ በፊት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የዘማች ቤተሰቦችን የመንከባከብና የመደገፍ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ሃላፊዋ፣ ሌሎች ድርጅቶችን በማስተባበር ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ አበባ ገበየሁ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመፋለም ወደ ግንባር በመሄዳቸው ኩራት የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለቤታቸውና ልጃቸው በድል እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልጸው የከተማ አስተዳደሩና የተለያዩ አካላት ለዘማች ቤተሰቦች እያደረጉ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም