''ሶሪያን ንደው ዜጎቿን እንደበተኑት ለመሆን አንፈቅድም"

69

ድሬዳዋ ህዳር 23/2014(ኢዜአ) ''ሶሪያን ንደው ዜጎቿን እንደበተኑት ለመሆን አንፈቅድም፤ ኢትዮጵያን ለማሻገር እንተጋለን'' ይላሉ አቶ ሰለሞን ተሰማ።

አቶ ሰለሞን በሞስኮ ኦሎምፒክና በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩ  የቀድሞ ታዋቂ ብስክሌተኛ ናቸው፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ልገሳና ስንቅ ዝግጅት ላይ ከተሳተፉ የድሬዳዋ አስተዳደር የስፖርት ቤተሰቦችና ሠራተኞች መካከል አንዱ ናቸው።

''ያለችውን አንዲት ነብስ ለሀገር ህልውና መረጋገጥ አሳልፎ እየሰጠ ለሚገኘው ጀግናው  የመከላከያ ሠራዊታችን ደሜን መስጠቴ ኢምንት ተግባር ነው '' ይላሉ አቶ ሰለሞን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።

''አካባቢዬን ከፀጥታ አካላት ጋር እጠብቃለሁ፤ ሀገር አፍራሹን የህውሃት ሽብርተኛ ቡድን ጥፋት ለማስቆም  ኃላፊነቴን በገንዘቤና በእውቀቴ እየተወጣሁ እገኛለሁ'' ብለዋል፡፡

"የሚያዋጣን አንድነታችንን አጽንተን ከውጭ ሀገራት ሚዲያዎች አሉባልታ ርቀን ሀገራችንን ከአሸባሪዎች ማዳን ብቻ ነው'' ሲሉም አከለዋል፡፡

''በየቀኑ ጋራዥ አካባቢ የሶሪያና የየመን ስደተኞች ህጻናት እጆች ለልመና ሲዘረጉ እመለከታለሁ፤ አንጀቴ ይንሰፈሰፋል፤ የትናንቷን ታላቋን ሶሪያ ማነው የናዳት፤ ለምን እላለሁ?''ሲሉም በመጠየቅ በምዕራባውያን ሴራ የፈራረሱትን ሀገራት ያነሳሉ።

''ሶሪያን ንደው ዜጎቿን እንደበተኑት ለመሆን አንፈቅድም፤ ኢትዮጵያን ለማሻገር እንተጋለን'' ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፡፡

''ጀግናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሀገር ህልውና መረጋገጥ ግንባር ዘምተው እኛ ዝም የምንልበት ህሊና የለንም''የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ሀገራችንን ከሽብርተኞች፣ አሜሪካን ጨምሮ ከአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ተንኮል ነጻ ለማውጣት መረባረብ አለብን'' ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሣሣይ ደም ለሠራዊቱ ሲለግስ የነበረው ወጣት አብዲ አፈንዲ ፤ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡

''የምንፈልገው ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጥቶን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ተሰልፈን ሀገር ማዳን ነው'' ብሏል፡፡

አሻበሪው ህወሃት ከድሬዳዋ ሕዝብ በላይ ያራቆተውና ያደኸየው አካል እንደሌለ በማውሳት ይህንን የጥፋት ቡድን ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ለመታገል  ማንኛውንም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ የገለጹት ደግሞ   በሠራዊቱ ስንቅ ዝግጅት የተሳተፉት ወይዘሮ ኮከቤ ምትኩ ናቸው፡፡

''ሀገርን ለማዳን እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግና ሠራዊት ደም ለግሰናል ፤ስንቅ ማዘጋጀቱን እስከ ጦርነቱ ፍጻሜ እንቀጥላለን'' ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ሰላም ኢብራሂም በበኩላቸው፤የሚፈልጉት ግንባር ድረስ ዘምተው የጨርቃጨርቅና የምድር ባቡር ድርጅትን አፍርሶ ድሬዳዋን ያደኸየውን አሸባሪውን ህወሃት ከሰራዊቱ ጋር በመሆን ለመታገል እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት፡፡

በዝግጅቱ ላይ ደም ከለገሱት መካከል የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት  ኮሚሽነር ፍራኦል ቡልቻ እንዳሉት፤በህልውና ዘመቻው የሚሳተፉ ሠራተኞችና የስፖርት ቤተሰቦች በሁሉም መስኮች አስተዋጽኦአቸውን እያጎለበቱ ነው፡፡

ወጣቶች ደም በመለገስ ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ገንዘብና አልባሳት በማሰባሰብና በአካባቢ ጥበቃ ተደራጅተው በደጀንነት የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጠንካራ አንድነት የሀገርን ህልውና ማረጋገጥ ትናንት ተጀምሯል፤ ዛሬ ፀንቶ ገዝፏል፤ ነገ ደግሞ በአሸናፊነት ያሻግራል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም