የወጣት ሴቶችን ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ተጋላጭነት ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ ነው

89

አዳማ፤ ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴት ወጣቶችን ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በስፋት ተጋላጭነት ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የክትባቶች ቡድን አስተባባሪ አቶ ተመስገን ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት ለቅድመ ወሲብ ካልደረሱት ጀምሮ በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ወጣት ሴቶች ላይ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እየታየ ነው።

በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴት ወጣቶች ለበሽታው በስፋት ተጋላጭ መሆናቸውን  የገለፁት አስተባባሪው ችግሩን ለመቀነስ ከትምህርት ዘርፍና መምህራን ማህበር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣት ሴቶች በስፋት ያሉበት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆኑን ጠቅሰው "በልዩ ትኩረት የመከላከያ ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ በግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ላይ በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል።

በተለይ ከ14  እስከ 40 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በስፋት ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን ክትባቱን በወቅቱ በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል አመልክተዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃረጓ ማሞ በበኩላቸው በየደረጃው ካለው የትምህርት ሴክተርና መምህራን ጋር የጋራ አደረጃጀትና ህብረት በመፍጠር በጋራ ለተማሪዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለይ ሴት ወጣቶችና ሴት ተማሪዎች  በሙሉ ክትባቱን እንዲያገኙ በማድረግ የበሽታውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል።

"የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢና የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የስርዓተ ፆታ ሃላፊ ወይዘሮ ፀሓይ ታደሰ ናቸው።

"እድሜያቸው ለወሲብ ያልደረሱ ልጃገረዶች  ጭምር ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆኑ ጥናቶች ያስረዳሉ" ያሉት ሃላፊዋ "ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ንቅናቄ ከመፍጠር ባለፈ ወጣት ሴቶች ክትባቱን እንዲወስዱ የማድረግ ስራ በየደረጃው ካሉ አደረጃጀቶቻችን ጋር እየሰራን ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

"ብዙውን ጊዜ ተማሪዎች ላይ የግንዛቤ ስራ ሳይሰራ ክትባቶች ቀጥታ ይሰጣሉ" ያሉት ወይዘሮ ፀሀይ  አካሄዱ ተማሪዎች ክትባቱን አምኖ መቀበልና  መከተብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በሚፈጠሩ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችና ጥርጣሬዎች ክትባቱን በሚፈለገው ደረጃ በመስጠትና በመውሰድ ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቅሰው በቀጣይ በተለይ ወጣት ሴቶች ክትባቱን እንዲወስዱ ርዕሰ መምህራንና መምህራን በማሳተፍ ጭምር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም