የአፋር ክልል ህዝብ ሀገሩን ለመጠበቅ እንደወትሮ ሁሉ አሁንም ዝግጁ ነው- አቶ አወል አርባ

59

ሠመራ፤ ህዳር 23/2014(ኢዜአ) የአፋር ክልል ህዝብ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ሀገሩን ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅ እንደወትሮ ሁሉ አሁንም ዝግጁ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በጥሬ ገንዘብና ዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

አስተዳደሩ ድጋፉን ዛሬ በሠመራ ከተማ ባስረከበበት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት አይደለም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብም አዘኔታ የለውም።

ለዚህም  በየግንባሩ በገፍ እያስገባ ለእልቂት የዳረጋቸው ታዳጊ ህጻናቶች ብቻ በቂ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ቡድኑ በሀገርና ህዝብ ላይ የሚፈጽመው ሴራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ኢትዮጵያዊያን  በቁጭት ተነስተው ግብአተ-መሬቱን እያፋጠኑት እንደሚገኙ አውስተዋል።

የአፋር ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጋር  በመቀናጀት  ሀገሩን ከወራሪዎች ለመጠበቅ እንደወትሮው ሁሉ አሁንም  ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው በክልሉ በፈጸመው የግፍ ወረራ ለችግር የተጋለጡ  የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፉ በቀጣይም እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ አኳያ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ለተፈናቃይ ወገኖች ያደረገው ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የህወሃት የሽብር ቡድን በተለይም በአፋርና አማራ የተለያዩ አካባቢዎች አሰቃቂ የግፍ ግድያና ዘርፊያ በመፈጸም በርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ  ይቅር የማይባል ክህደት በሀገርና ህዝብ ላይ ፈጽሟል ያሉት ከንቲባው፤ አስተዳደሩ በአሸባሪው ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲውል የ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

ከድጋፉ ወስጥ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር  የሚገመቱ  የተለያዩ ምግብ ነክ ቁሶች ሲሆኑ፤ ቀሪው በጥሬ ገንዘብ አስረክበዋል።

የአፋር ክልል ህዝብ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን የአሸባሪውን  ቡድን ሴራ ለማክሸፍ ሀገራዊ ግዴታውን መወጣቱን እንዲያጠናከርና የተጎዱ ወገኖችን መልሶ እስከ ማቋቋም ድረስ  ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ከንቲባ ከድር አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም