በደቡብ ክልል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ 300 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

76
ሃዋሳ ነሀሴ 17/2010 በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ግርግር ለማስወገድ በተካሄደው ህብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ግጭት ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደቀደመው ሰላማቸው  መመለሳቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ 300 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል እንደገለጹት በሀገርና ክልል ደረጃ ከመጡ ለውጦች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት ለመቀልበስ  ህዝቡን ያሳተፈ ስራ ተከናውኗል፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሁሉም አካባቢዎች ሰላሙን ወደ ነበረበት የመመለስ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ በሀገርና በክልል ደረጃ አሁን ያሉ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ህዝቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡ በዚህም በክልሉ ከነበረው የጸጥታ ስጋት አንጻር በአሁኑ ጊዜ አበረታች ለወጥ እየመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከተፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ በጋሞጎፋ ዳውሮ፤ በካፋና ሸካ ዞኖች የተፈጠረው አለመረጋጋት ወጣቱንና ሌላውን የማህበረሰብ ክፍል በማወያየት ወደነበረበት ሁኔታ የመመለስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ንብረት እንዲወድምና ወደ አመጽና ሁከት እንዲገባ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 300 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ መስፈኑንና ህዝቡም ወደ ዘወትር ስራ መመለሱን ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ጨለማን ተገን በማድረግ በዝርፊያና ንጥቂያ ላይ የተሰማሩ አካላትን በመረጃ በማስደገፍ በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን ህግ የማስከበር ስራ ለማጠናከር ህብረተሰቡ ከህግ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም