ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ለመከላከያ ሰራዊት 10 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረጉ

57

መቱ ሕዳር 23/2014 (ኢዜአ): የኢሉ አባቦር ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ለመከላከያ ሰራዊት 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ድጋፍ አደረጉ።
የዞኑ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው በሚቀጥሉበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

የዞኑ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ በፍቃዱ ገምቴሳ በወቅቱ እንደገለፁት ባለሀብቶቹና ነጋዴዎቹ ሁሉን ማድረግም ሆነ መሆን የሚቻለው ቅድሚያ ሀገር ስትኖር ነው በሚል  ለህልውና ዘመቻው የሚያደርጉትን ድጋፍ ቀጥለዋል።

የህብረተሰብ ክፍሎቹ ከዚህ ቀደም ለህልውና ዘመቻው ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ በቅርቡ ከመንግስት የተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ድጋፍ ማድረጋቸውን የቀጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"የሀገር ጉዳይ የፓርቲ ወይም የመንግስት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ የንግዱ ማህበረሰብ ይገነዘባል" ያሉት አቶ በፍቃዱ ለሰራዊቱ የክተት ጥሪውን ተከትሎ ከነጋዴዎችና ባለሀብቶች በድጋፍ የተሰበሰበ 9 ሚሊዮን 873 ሺህ 374 ብር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ከነጋዴዎች መካከል አቶ አንዳርጌ ጎበና በበኩላቸው "ሰርተን ማግኘትም ሆነ  ነግደንም ማትረፍ የምንችለው ሀገር ስትኖር በመሆኑ የሀገር ሕልውናን ለመታደግ የማይውል ሀብትም ሆነ ንብረት አይኖረንም" ብለዋል።

"በዚህ ፈታኝ ጊዜ ሀገር ለማሻገር የማይቆምና የማይሰጥ ሀብታም ሀብቱ ትርጉም የለውም" ያሉት ደግሞ አቶ ተሰማ በጨራ ናቸው።

"በሀገር የመጣ ሁሉ የመጣው በእኛና በሀብት ንብረታችን ጭምር መሆኑን ልብ ልንልና ሕልውናችንን ለማረጋገጥ ባለን አቅም ሁሉ መረባረብ ይኖርብናልም" ብለዋል።

የኢሉ አባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ "ባለሀብቶችና ነጋዴዎች የሀገር ሕልውናን ለማስከበር ያደረጉት አስተዋፅኦ እንደ ድጋፍ የሚታይ ሳይሆን ከሀገር ወዳዶች የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ተደርጎ መታየት አለበት" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም