በሀዋሳ ከተማ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

162

ሀዋሳ ፤ ህዳር 23/2014( ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በመኖሪያ ቤቶችና መጋዘን በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የተለያዩ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ከነተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው አባልና የአስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ደረሰ ቡሳኖ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ ትናንት ምሽት በተደረገ ድንገተኛ ፍተኛ  ሽጉጦች፣ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ፣ የጦር ሜዳ መነጽርና ሌሎች የስለት መሳሪያዎች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ፣ ፓስፖርቶች፣ የባንክ የሂሳብ ደብተሮችም እንዲሁ።

ከእነዚህም የተለያዩ ፓስፖርቶችና  የባንክ  ቼኮች በአንድ ሰው ስም  የወጡ መገኘታቸውን አስረድተዋል።

በከተማዋ የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ የአባላት ምልመላ ና የሚፈጽሙትን  ዝርዝር የያዙ ሰነዶችም መገኘታቸወንም ምክትል ኮማንደሩ አመላክተዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ  የተጠረጠሩ  ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።