ማህበሩ ለመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

99

ጎንደር፤  ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር በህልውና ዘመቻው በግንባር ለተሰለፉ የፀጥታ ሃይሎች የሚውል ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በጥሬ ገንዘብና ዓይነት ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ የሰው ሃይል አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ አምባው ድጋፉን ዛሬ ለጎንደር ከተማ ሃብት አሰባሳቢ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለመሻገር መደጋገፍ የግድ ነው።

በዚህም ለስንቅ ዝግጅት እንዲውል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 200 ኩንታል የዳቦ  ዱቄት ድጋፍ አበርክተዋል።

በተጨማሪም በ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ የቴምር፣ ብስኩት፣ አልባሳትና ጨማ ድጋፎችን በጠለምት ግንባር ለሚገኘው የጸጥታ ሃይል እንዲውል መላኩን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ የተሰባሰበው ከአክስዮን ማህበሩ በጀት እንዲሁም ከሠራተኞችና አመራር አባላት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አክስዮን ማህበሩ ሀገራን ለማዳን እየተካሄደ ባለው ትግል የሚሳተፉ አስር ሠራተኞችን ወደ ግንባር መላኩንና ተጨማሪ 20 ሠራተኞችም ለመዝመት እየተጠባባቁ እንደሚገኙ አስታወቀዋል።

ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም በወራሪው ህወሓት የወደሙትን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ አክስዮን ማህበሩ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የህልውና ዘመቻው አስተባባሪ አቶ ዘውዱ ማለደ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ፤የዳሽን ቢራ አክስዮን ማህበር ሁሌም ከጎናቸው ያልተለየ አጋራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ ከተማ አስተዳደሩ ለሚያካሂደው ሰፊ የስንቅ ዝግጅት እንዲውል ያደረገው የገንዘብና የዳቦ ዱቄት ድጋፍ ለስንቅ ዝግጅቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአክሰዮን ማህበሩ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም