ኢትዮጵያን መጠበቅና ሉዓላዊነቷን ማስከበር የመላውን ሕዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው

76

ህዳር 23 / 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ሳይሆን የመላውን ሕዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።
ምክትል ከንቲባው የመከላከያ ሠራዊቱን ለማበረታታት እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ያዘጋጀውን የዕለት ደራሽና አልሚ ምግብ ለማስረከብ በግንባር ተገኝተዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በማክሸፍ በድል እየገሰገሰ ይገኛል።

አቶ ጃንጥራ አባይ ለመከላከያ ሠራዊቱ በድል የታጀበ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደጀን ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መላው የአዲስ አበባ ሕዝብም በሁሉም መስክ መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው ኢትዮጵያን መጠበቅ፣ እንዳትፈርስ ማድረግ የመከላከያ  ሠራዊቱ  ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ሠራዊቱ ከሚያስመዘግበው ድል በስተጀርባ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነፃና ሉዓላዊት አገር መሆኗ እረፍት የነሳቸው ጠላቶቿ ትናንትም እንደነበሩ ገልጸው ዛሬም በተባበረ ክንድ ነፃነታችንን እናስከብራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም