የጌዴኦ ባህላዊ መሪዎች አሸባሪው ህወሓት በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግፍ አወገዙ

142

ዲላ፤ ህዳር 23/2014 (ኢዜአ) የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያውያን እምነት፣ ባህልና ሥርዓት ውጭ የፈጸማቸውን ግፎች አጥብቀው እንደሚያወግዙ አስታወቁ።

መሪዎቹ ለሀገር ሰላም ምልጃና በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመው ግፍ የሚያወግዝ ባህላዊ የ"ፋጭኤ" ስርዓት በአባገዳ መናገሻ በኦዳ ያአ ሶንጎ ትናንት አካሂደዋል።

የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ የባሌ አስተዳደር መሪ አባ ገዳ ዳንቦቢ ማሮ  በወቅቱ እንዳሉት፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግጭቶች ሲከሰቱ የሰው ልጆችን ክብርና የተፈጥሮ ህግ ማክበር ግዴታ ነው።

ሆኖም በህወሓትና የጥፋት ተላላኪዎቹ የሚፈጸሙ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ከኢትዮጵያውያን ባህልና ስርዓት በእጅጉ ያፈነገጡ ከመሆናቸው ባለፈ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።

በተለይ ንጹሀንን መግደል፣ ሴቶችና ህጻናትን መድፈር ፣ንብረትን ማውደም በትውልድ መካከል ቁርሾን ከማስቀመጥ ባለፈ የፈጣሪን ቁጣ እንደሚቀሰቀስ ገልጸዋል።

በጌዴኦ ባህል ሰውና እንስሳትን ቀርቶ ዛፍ ያለአግባብ መቁረጥ ሃጥያት ነው ያሉት አባ ገዳው፣ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ባህልና ስርዓት ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት እንደሚወገዙ አስታውቀዋል።

ባህላዊ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች አካባቢያችንን በንቃት ከመጠበቅ በተጓዳኝ ፈጣሪ ለሀገራችን ሰላም እንዲያመጣ በጾምና በጸሎት መትጋት አለብን ብለዋል።

አጥፊውን ቡድን በሀሳብም ሆነ በተግባር ከመደገፍ ልንቆጠብ ይገባል የሚሉት ደግሞ ሃይቻ አለማየሁ ሂሪቤ ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት  በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ያወገዙት ሃይቻ አለማየሁ፤ በተለይ ለሸኔ ከለላ የሚሰጡ አካላት እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ሀገራችንን ከማፍረስ ባለፈ ባህላችንና  ኢትዮጵያዊነታችንን ለማጠልሸት የተነሱብንን የጥፋት ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሴቶችን የሚደፍሩ፣ እንስሳትንና ሰብልን የሚያወድሙትን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጥፍተን ወደ ልማትና ሰላም መመለስ ይገባናል ብለዋል።

የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ እጩ ዶክተር የሴፍ ማሩ በበኩላቸው፤ የጌዴኦ ባህላዊ አባቶች በሀገር ላይ  ሰላም ሲታጣና ድርቅ ሲከሰት ባህላዊ የምልጃና የጸሎት "ፋጭኤ" ስርዓት እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።

ዛሬም ከምልጃው በተጓዳኝ በአሸባሪው ህወሓትና በጥፋት ተባባሪዎቹ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በአጭር ጊዜ እንዲቆሙ በጋራ መነሳት እንዳለብን ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ በባህላዊ ስርዓት የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩም ሃላፊው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም