ለመተከል ሰላም ቀጣይነት ከመከላከያ ጎን በመቆም አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንከፍላለን - የወምበራ ወረዳ ነዋሪዎች

67

አሶሳ ፤ ህዳር 23 / 2014(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተገኘው  ሠላም በዘላቂነት እንዲቀጥል ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ በዞኑ የወምበራ ወረዳ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
ነዋሪዎቹ የሃገር መከላከያ ሠራዊትን በመደግፍ፣ የዞኑን ሠላም ሲያውኩ የነበሩ የሽብርተንቹኔ ህወሃት ና ሸኔን ታላላኪዎች እንዲሁም የጉሙዝ ታጣቂን በማውገዝ በወረዳው ደብረዘይት ከተማ ሰልፍ አካሄደዋል፡፡

በሰልፉ ከተሳተፉት መካከል አቶ ገመቹ ማራ እንዳሉት፤አሸባሪው የህወሃት ቡድን ተላላኪዎች  በፈጠሩት  የጸጥታ ችግር በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

የጸጥታ ሃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት በአሁኑ ወቅት ወምበራ ወረዳን ጨምሮ መተከል ዞን ወደ መረጋጋት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሁለት ልጆቻቸው ሀገርን ለማዳን እየተካሄደው ባለው ትግል ለመሳተፍ የህልውና ዘመቻውን መቀላቀላቸውን  ያወሱት አቶ ገመቹ ፤ የዞኑ ሠላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል  አካባቢያቸውን በመጠበቅ የድርሻቸውን እየተወጡ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  መከላከያ ሰራዊትን   በግንባር ተገኝተው መምራታቸው ለአካባቢው ህብረተሰብ ሞራል እንደሆነ  አመልክተዋል፡፡

የቀድሞው የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበሩ ያስታወሱት ነዋሪው፤ አሁንም የሃገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል አስፈላጊው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ነው ያመለከቱት፡፡

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት መልካሙ ታደሰ፤  አሸባሪው የህወሃት ቡድንን የጥፋት ድርጊት በማስቆም   ሃገርን ማስቀጠል ለኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ ነው ይላል፡፡

በወረዳው የሽብር ቡድኑ ተላላኪ ርዝራዦች  የመተከል የጸጥታ ስጋት እንዳይሆኑ አካባቢአችንን ነቅተን እየጠበቅን ነው እንገኛለን ሲል ገልጿል፡፡

ባለን አቅም ሁሉ የመተከልን ሠላም ማስቀጠል አለብን፤ ለሃገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎችንም የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረግን እገኛለን ብሏል፡፡

የአሸባሪው   ህወሃት ተላላኪዎች መተከልን ማዕከል አድርገው  ሃገር ለማፍረስ በጠነሰሰው ሴራ የወረዳው ህዝብ ተጠቂ እንደነበር በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ  የወረዳው ሚሊሻ አዛዥ አቶ ቢኒያም ግዛቸው ናቸው።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን በመምራት በሽብር ቡድኑ ላይ ከሰሞኑ እየተመዘገበ የሚገኘው ድል ህብረተሰቡ ይበልጥ በመነቃቃት አካባቢውን በበለጠ እየጠበቀ  ነው ብለዋል፡፡

መተከል ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ሠላሟ እስክትመለስ የወረዳው ሚኒሻ አባላት ባላቸው አቅም ሁሉ ከሃገር መከላከያ እና ልዩ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ አቅም የሌላቸው መዝመት የማይችሉ የወረዳው ነዋሪዎችም ያላቸውን ትጥቅ ለወጣቱ በማስረከብ ለዞኑ ብሎም ለሀገር ሠላም ቀጣይነት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የወምበራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ አዲሱ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ፤ ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ኢጣሊያን መክተው የመለሱት በጠንካራ አንድነታቸው እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ሽብርተኛው ህወሃት የኢትዮጵያውያን አልበገር ባነይት ሚሲጥር የሆነውን ህዝባዊ አንድነትን ለማጥፋት ለረጅም ዓመት ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ  በመተከል ዞንም ወምበራ ወረዳ የጉሙዝ እና ሸኔ ታጣቂዎችን በማሠማራት በነዋሪዎ ላይ በፈጸመው ጥቃት ያደረሰውን ጉዳትም ጠቅሰዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡

በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ ሠላም እና መረጋጋት መመለሱን ጠቁመው፤ የሽብር ቡድኑ መተከልን ማዕከል ያደረገ ሃገር የማፍረስ እቅድ መክሸፉን አስረድተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ከወረዳው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጽዳት አስተዳደሩ  የጸጥታ ሃይሉ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጥረት እያረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡም በተለይ ተደራጅቶ አካባቢን በመጠበቅ ለሠራዊቱ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ እንዲያጠናክር አቶ ሙሉጌታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የወረዳው ነዋሪዎች የደረሱ ሰብሎችን በደቦ በመሰብሰብ የተመረተው ሰብል እንዳይባክን ማድረግ ሌላው ትኩረት መስጠት ያለባቸው ጉዳይ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡

በሰልፉ ላይ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎችም  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን  ኢዜአ  ከወምበራ ወረዳ የኮሙዩኒኬሽን  ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም