የምዕራብ ወለጋና የነቀምቴ ከተማ ሴቶች ለሰራዊቱ የስንቅ ድጋፍ አደረጉ

71

ግምቢ/ነቀምቴ ህዳር 23/2014(ኢዜአ) የምዕራብ ወለጋና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የስንቅ ድጋፍ አደረጉ።

በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉ ሴቶች እንዳሉት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተፋለመ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ ከማዘጋጀት ባለፈ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጥቂት የሽብር ቡድኖችና በአንዳንድ  የውጭ ተባባሪዎቻቸው  ብትፈተንም ጀግና እና የቁርጥ ቀን ልጆች ስላሏት መቼም አትፈርስም ብለዋል ሴቶቹ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፀሐይ ኤቢሳ እንደገለጹት የዞኑ ሴቶች ለሠራዊቱ ስንቅ ያዘጋጁት ከዞኑ ሴት የመንግስት ሠራተኞች ጋር በመተባበር ነው፡፡

የዞኑ ሴቶች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 70 ኩንታል ደረቅ ስንቅ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አዘጋጅተዋል።

ከዚህም ባሻገር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል ከ931 ሺህ 400 ብር በላይ አሰባስበዋል ብለዋል፡፡

የሀገር ህልውና እያስከበረ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅ ከመዘጋጀትም ባለፈ ለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት  ወደ አውደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

ወይዘሮ መሰሉ ደረጀ እንዳሉት ሁሉም በሰላም መኖር የሚችለው ሀገር ሰላም ስትሆን ስለሆነ ለሰራዊታችን ደጀን ከመሆን በላይ አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን ግንባር ለመፋለም ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ለሀገር ሉዓላዊነት ውድ ህይወቱን እየገበረ ላለ ሰራዊታችን በሁሉም መስክ ከጎኑ እንቆማለን ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ታሪኳ ኤባ ናቸው።

በተመሳሳይ ዜና የነቀምቴ ከተማ ሴቶች ከ86 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ከ11 ኩንታል በላይ ስንቅ ማዘጋጀታቸውን የከተማው የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰንበቴ ደረጀ ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ዳግም የሕዝብ ስጋት እስከማይሆኑ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የከተማዋ ሴቶች በመጀመሪያው ዙርም 187 ሺህ ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎችን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ማድረጋቸውን ኃላፊዋ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም