የ "#በቃ" ወይም '#No More' ዘመቻ አካል የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች በአውሮፓ፣እስያና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች በሚገኙ ከተሞች ከሕዳር 24 እስከ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ይካሄዳሉ

114

አዲስ አበባ ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ "#በቃ" ወይም '#No More' ዘመቻ አካል የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች በአውሮፓ፣እስያና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች በሚገኙ ከተሞች ከሕዳር 24 እስከ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ይካሄዳሉ።

ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ከነገ በስቲያ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

የሰልፉ አዘጋጅ የኢትዮ-ጀርመን ግብረ-ሃይል በሰልፉ በጀመርን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፣ኤርትራውያን፣የአፍሪካ አገራት ዜጎችና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተጨማሪ በፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ቅዳሜ ሕዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ የሚያደርጉትን ጫና የሚቃወም ሰልፍ በፓሪስ ከተማ ያካሄዳሉ።

ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የከፈታቸውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳና የአሸባሪው ሕወሓት የሽብር ተግባራት የሚያወግዙ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ የሰልፉ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።

'እኔ የአባቶቼ ልጆቼ ነኝ' በሚል መሪ ሀሳብ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁት ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ እሁድ ሕዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በቤይሩት ከተማ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱ ውጫዊ ጫናዎች የሚቃወሙና "የራሳችንን ችግሮች በራሳችን እንፈታለን" የሚሉ መፈክሮች ሰልፈኞቹ እንደሚያሰሙ ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሰልፉ ላይ በሊባኖስ የሚኖሩ ኤርትራውያን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በተያያዘም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነነት የሚቃወም ሰልፍ እሁድ ሕዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

በሰልፉ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፣ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሽንግተን ዲሲ ገብረ ሃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የተሳሰተ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እስክታስተካክል ድረስ ሰልፉ በቋሚነት የሳምንቱ እሁድ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ መካሄድ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በተያያዘም የበቃ ወይም '#No More' ዘመቻ አካል የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች በቀጣዩ ሳምንት በአውስትራሊያ ሲድኒና በጃፓን ቶኪዮ ከተሞች ይካሄዳል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በሚኒሶታ ግዛት ትናንት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄዷል።

በሰልፉ ላይ በሚኔሶታ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳታፊ ሆነዋል።

ሰልፉ የተዘጋጀው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በሚኒሶታ ግዛት ዳኮታ ካውንቲ ቴክኒካል ኮሌጅ ያደረጉትን የስራ ጉብኝት ተከትሎ ሲሆን ሰልፈኞቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው ቴክኒካል ኮሌጅ በማቅናት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በተያያዘም የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጨውን ሐሰተኛ ዘገባ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ አትላንታ በሚገኘው የጣቢያው ማዕከል እየተካሄደ ነው።

የ "#በቃ" ወይም '#No More' ዘመቻ አካል የሆነ ዓለም አቀፍ ሰልፍ ሕዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም በ31 የዓለም ዋና ዋና ከተሞች ላይ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም