አድማሱን ያሰፋው #NoMore ንቅናቄ

128

በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ  ሁለተኛ፤ በቆዳ ስፋት አስረኛ የሆነችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ምደረ ቀደምት አገር  ኢትዮጵያ ብቸኛዋ  ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረች  የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት፡፡  ኢትዮጵያ የአውሮፓ መንግስታት ተስፋፊነት የወለደው የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ተቃውማ በመነሳት ዓድዋ ላይ የጣሊያንን ቅኝ ገዥ ወራሪ ሰራዊት ገጥማ ድል በመንሳት የአንፀባራቂ ታሪክ ባለቤት መሆን የቻለች አገር ናት፡፡ ይህም  አንጸባራቂ የድል ገድሏ ለመላው  አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ባርነት ነጻ ለመውጣት የሚያስችል ትግል እንዲያካሂዱ ከማነሳሳቱም ባለፈ ለነጻነት ታጋይ አፍሪካዊያን ወንድሞች ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል፣ ነጻነትና መብት መከበር ባደረገችው ደማቅ አኩሪ ታሪክ የምትታወቅ አገር ናት፡፡

ለአብነትም የፀረ አፓርታይድ ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን አሰልጥና በማስታጠቅ ለደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ነፃነት ትግል ያካሂድ ዘንድ ኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጓ የሚታወቅ ነው፡፡ ከኔልሰን ማንዴላ በተጨማሪ የሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎር፣ የኬኒያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬኒያታና  የዛሬዋን የዚምባብዌይ ህዝቦች ከተመሳሳይ የጥቂት ነጮች ጨቋኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የታገሉትን ሙጋቤንና ጓደኞቻቸው በኢትዮጵያ ሰልጥነው ወይም ሌላ ድጋፍ ተደርጎላቸው ውጤታማ የነጻነት ትግል ማድረግ የቻሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊያን ከአራቱም ማዕዘናት ተጠራርተው በመዝመት እንደሌላው አፍሪካዊ ህዝብ በኃይል አንበርክኮ ቅኝ ሊገዛቸው የመጣውን አውሮፓዊውን የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ ድባቅ በመምታት መላውን ዓለም ያስደመመ ታምራዊ የድል አድራጊነት ታሪክ የሰሩበትን የነፃነት ገድል ሊያገኙ የቻሉበት ሚስጢር በመላው አገሪቱ የሚገኙ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ በመሆን ለቅኝ ገዥ ያለመንበርከክ የኢትዮጵያዊ የጀግንነት ስሜት መላበስ ሲሆን ይህም ድል የማድረግ ስሜት ወደ ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች ጭምር እንዲጋባ   በመፈለግና በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያኒዚም እንቅስቃሴ በመፍጠርና ወደ ፓን አፍሪካኒዚም ማሳደግ በመቻሉ የአፍሪካ ነጻነት ሊረገገጥ ችሏል፡፡

ቅኝ ገዥዎች ያለሙትንና የቋመጡለትን በኃይል የአፍሪካን አገራትና ህዝቦች በመቆጣጠር፣ በማንበርከክ የጉልበትና የሃብት ብዘበዛ፣ የባህል ወረራና የመብት ረገጣ የማድረግ ፍላጎት በኢትዮጵያኒዝምና በፓን አፍሪካኒዚም የአርበኝነት ተጋድሎ ምክንያት አልተሳካልንም ብለው አርፈው አልተቀመጡም፡፡ ይልቁንም ምቹ ወቅትና ጊዜ በመጠበቅ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የተለያዩ  ስልቶችን በመንደፍ የተለያዩ  ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በማንበርከክ አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት የውስጥና የውጭ ባንዳዎችን እንደ ግብ ማሳኪያ መሳሪያ የመጠቀም ስልት በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ትግል እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በሴራ የጀመሩት  ትግል በከፍተኛ ሁኔታ አድጎና አይሎ በይፋ እየታየ ይገኛል፡፡ ይህን የተረዱ በኢትዮጵያና በመላው አለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆቻ በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት የሚያሴሩትን የምዕራቡ ዓለም አገራትን፣ የውጭና የውስጥ ባንደዎችን "እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" በማለት አይበገሬነታቸውን ለማሳየት በቆራጥነት ተነስተው ዘመናዊ ትግል እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

‘እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ’ የንቅናቄ ጅማሮው ኢትዮጵያ በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚደፈር የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን አለመኖሩ የፈጠረው ቁጭት ሲሆን በዚህን ንቅናቄም  የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሆነው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙበት መርሃ ግብር በግንቦት ወር መጀመሪያ በ2013 ዓ.ም ተጀምሮ አለምን ለማዳረስ ችሏል፡፡

ይህ ንቅናቄ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሆነው ለአንድ ሠዓት መልዕክታቸውን ያስተላለፉበት ሲሆን የመጀመሪያው  መርሃ ግብር የተካሄደው በኢትዮጵያ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡  በኋላም ዜጎች በያሉበት ሆነው ለአገራቸው ሉአላዊነት መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መልዕክት ለመላው አለም ያሳዩበት ታላቅ ኹነት ሆኖ ያለፈ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ "በቃ"  የሚል ንቅናቄ ተጀመሮ አድማሱን በመላው አለም  እያሰፋ ይገኛል፡፡

ይህ ንቅናቄ  ልክ እንደ ትናንቱ አድዋ ዛሬም “ብሔራዊ ክብር በሕብር” የሚል ስያሜ ያለው  ነው፡፡ ንቅናቄው  የተዘጋጀውም በማሕበረሰብ አንቂዎች፣ በአርቲስቶች፣ በሲቪክ ማሕበራትና ታዋቂ ግለሰቦች ሲሆን በዋነኝነትም “ግድቡ ገንዘቤ፣ ዓባይ ወንዜ!፣ ዓባይ ጸጋችን ነው፣ ኢትዮጵያ አትደፈርም አንንበረከክም” የሚሉ መልዕክቶች በተሰካ መልኩ ለአለም ማህበረሰብ ማስተጋበት ያስቻለ ንቀናቄ ሲሆን “ክብርና ሉዓላዊነታችንን አትንኩ የምንለው በአያቶቻችን መስዋዕትነት የታፈረች፣ የተከበረች እና በዋጋ የተረከብናት አገር በመሆኗ ነው” ሲሉ  ሚሊዮኖች ድምጻቸውን ለማሰማት ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

ከላይ እንደተገለጸው፤ ኢትዮጵያ በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ዜጎች ኢትዮጵያ በዘመነ ክብሯ ሉዓላዊነቷን የሚደፍር የትኛውንም ኃይል አሜን ብላ የተቀበለችበትና ያጎነበሰችበት ዘመን እንዳልነበረና ወደፊትም እንደማይኖር አስረግጠው መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ኢትዮጵያ “ከራሷ አልፋ ለሌሎች ነፃነትን ያስተማረች፤ አልገዛም ባይነትን በተግባር ያሳየች፤ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር በመሆን መታወቋ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በንቅናቄውን እንዲሳተፉና አድማሱን እንዲያሰፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ሰአት ከአፍሪካዊያን በተጨማሪም መላውን ጥቁርና ምዕራባዊያንን ጨምሮ ሌሎች የአለም አገራትና ታዋቂ ግለሰቦችን ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን #NoMore ንቅናቄን እየተቀላቀሉት ይገኛሉ፡፡ 

ንቅናቄውን ከተቀላቀሉት  ታዋቂው ግለሰቦች መካከል እንግሊዛዊው ፓል ሬይኖልድስ አንዱ ሲሆኑ ንቅናቄውን በተቀላቀሉበት ወቅትም 2 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ የፈጀ አጭር የቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልክታቸውም እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ያሉና ሌሎችም የምዕራብ አገር መንግሥታት  በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥትና ከ115 ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎት ጋር እየተቃረኑ፤ በሉኣላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትም ከባድ ስህተትን እየፈፀሙ ነው ሲሉ በይፋ ተችተዋል።

ግለሰቡ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ በማለት የኢትዮጵያን ሙሉ እውነት የገለጡበትን የቪዲዮ መልዕክታቸውን መደምደማቸው የሚታወስ ነው። ከእንግሊዛዊው ፓል ሬይኖልድስ በተጨማሪ  አፍሪካ አሜሪካዊው የሙዚቃ አቀንቃኝ ኤኮን፣ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር እና ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንይን የአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴናተር ሼላ ጃክሰንም ንቅናቄውን ከተቀላቁሉት መካከል ይገኙበታል፡፡ ከነዚህም ታዋቂ ሰዎች በተጨማሪም የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያስተካክልና ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም ጫና ለማድረግ ሰላማዊ ሰልፉ በዋሺንግተን ዲሲ በቋሚነት በየሳምንቱ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቆ ይገኛል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶችና ማህበራት በንቅናቄው በመሳተፍ የኢትዮጵያን እውነት በማሳየት ረገድ አመርቂ ውጤትና ተቀባይነት እያስገኙ ነው፡፡

በኢትዮጵያዊያን የተጀመረውና ተቀባይነትን ያገኘው፣ በርከቶች የተቀላቀሉት የፀረ Neocolonialism የ #Nomore ንቅናቄ  አድማሱን አስፍቶ በአፍሪካ ሀገራት ተጠናክሮ ቀጥሏል። ንቅናቄውን በውጭ የሚገኙ ኤርትራዊያን ቀድመው ከኢትጵያዊያን ጋር የጀመሩ ሲሆን በቡርኪናፋሶ ደግሞ የዘመናዊ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ወታደሮች "በሰላም አስከባሪ ስም አሸባሪዎችን በማገዝ እያጫረሱን ነው በቃን #Nomore ውጡልን !!" በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ይህ ንቅናቄ ወደ ማሊና ኒጀር በአሁኑ ሰአት ደርሶ ይገኛል። ከዚህም በላይ አሜሪካ እና የምዕራባውያኑ ሚዲያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ታዓማኒነት እንዲያጡ አድርጓል፡፡ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንጂ ከምዕራቡ ዓለም እየተሰፈረ የሚሰጥ መፍትሄ አፍሪካን ለድህነት እንጂ ለብልጽግና አለማምጣቱን በሰፊው ግንዛቤ የማስያዝ ውጤት አምጥቷል፡፡ አሜሪካና ምዕራባውያኑ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን በማንበርከክ የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ መሆኗ እንዲቀር የሚያሴሩት ሴራ እየከሸፈና ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ንቅናቄ አድማሱን እያሰፋ ይገኛል። ንቅናቄው አላማውን ሙሉ በሙሉ እስከሚያሳካ ድረስ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም