በማህበር ለተደራጁ ከ1 ሺህ 900 በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል- ጽህፈት ቤቱ

67

ጅማ፣ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) በጅማ ከተማ በማህበር ለተደራጁ ከ1 ሺህ 900 በላይ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የከተማው የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ወጣቶቹ በ335 ማህበራት ተደራጅተው በከተማ ጽዳት፣ በልብስ ስፌት፣ በከተማ ግብርና፣ በከተማ ውበት ጥበቃና በተለያዩ የንግድ ስራዎች መሰማራታቸውን የከተማው  የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ የዚድ አባገሮ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ በህዳር ወር 2014 መጀመሪያ የ300 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲሁም  የማምረቻና ንግድ ቦታ ተመቻችቶላቸው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በከተማ ጽዳት ለተደራጁ ማህበራት የእጅ ጋሪ፣ በከተማ ግብርና ለተደራጁ ትራክተር መሬትና በተለያዩ የንግድ ስራዎች ለተሰማሩ ደግሞ ሼዶችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አቶ የዚድ አስታውቀዋል።

ወጣት ዘሀራ ተማም በከተማ ጽዳት የተደራጀች ሲሆን ከማዘጋጃ ቤቱ አጋዥ መሳሪያዎችን አግኝተው ወደ ስራ እየገቡ መሆኑን ተናግራለች።

ወጣት ከድር አባመጫ እንዳለው ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በከተማ ጽዳት ተደራጅተው በተደረገላቸው የስራ መሳሪያዎች ድጋፍ ወደ ስራ ገብተዋል።

አባላቱ ጠንክረው በመስራት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማደግ ተስፋ ይዘው እየተጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"ከጓደኞቼ ጋር በከተማ ግብርና ተደራጅተን በተደረገልን ድጋፍ ታግዘን ወደ ስራ ገብተናል" ያለው ደግሞ ወጣት መሀመድ ከማል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም