ቻይና ለአፍሪካ አገራት ለመጀመር ያሰበችው ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል "ግሪን ሌን" አፍሪካዊያንን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው

76

ህዳር 22/2014(ኢዜአ) ቻይና ለአፍሪካ አገራት ለመጀመር ያሰበችው ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል "ግሪን ሌን" አፍሪካዊያንን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አንድ የኢኮኖሚ ምሁር ተናገሩ።

የአፍሪካ አገራት የግብርና ምርታቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲልኩ አሜሪካ ያመቻቸችው (አጎዋ) የገበያ አድል በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉ ይታወቃል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት አገራት እድሉን እንዳይጠቀሙ መወሰኑ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ተገቢነት እንደሌለው በርካታ የዘርፉ ምሁራን በመግለፅ ኢትዮጵያ ሌሎች የገበያ አማራጮችን እንድታመማትር አመላክተዋል።

ቻይና ለመጀመር ያሰበችው የአፍሪካ አገራት የግብርና ምርታቸውን ከቀረጥ ነጻ የሚያቀርቡበት የገበያ አማራጭ "ግሪን ሌን" ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎችም የአፍሪካ አገራት ጥሩ ተስፋ ይዞ የመጣ መሆኑን ምሁራኑ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በተለይም በእንስሳት ሃብትና በግብርና ምርት የመልማት ሰፊ እድል ያላት ሲሆን በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪም ተጠቃሚ ለመሆን በስፋት እየሰራች ትገኛለች።

ለዚህ ደግሞ አማራጭ የገበያ መዳረሻዎች ስለሚያስፈልጉ ቻይና ይዛው ብቅ ያለችው አዲስ እሳቤ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርጋት እንደሚችል ይታመናል።

በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያከናወነች ያለቸው ቻይና ለአፍሪካ የግብርና ምርት ልታመቻቸው ያሰበችው ከቀረጥ ነጻ ግብይት "ግሪን ሌን" ጉልህ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ኢዜአ ያነጋገረው ኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ይናገራሉ።

የኢኮኖሚ መሰረቷን በግብርና ላይ አድርጋ የዜጎቿን ህይወት ለመቀየር የምትተጋውን ኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው ያሉት።

''ምዕራባውያን ለረጅም ዓመታት አፍሪካን ጫና ውስጥ የሚከቱ ተጽዕኖዎችን ሲፈጽሙ የቆዩ ናቸው'' ይላሉ ዶክተር ተሾመ።

ምዕራባውያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከተሉት አካሄድ 'ደሆች' በድህነታቸው እንዲቀጥሉ 'ሀብታሞችም' ሀብታቸው እንዲጨምር ነው ሲሉም ያብራራሉ።

እቅዳቸው እንዲሳካ የተለያዩ ተቋማትን አሰማርተው በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ዘርፎች ተዕጽኖ እያሳረፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ የአፍሪካ አገራት ከድህነት አዙሪት እንዳይወጡ በተከታታይ ተለዋዋጭ መልክ ያለው ጣልቃ ገብነት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ አሁን እያደረጉት ያለው ተጽኖና ጣልቃ ገብነት ከዚሁ እሳቤ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው ጥሩ ነገሩ በዚህ ዘመን ዓለም በአንድ ሃይልና እሳቤ ከመመራት ወደ ብዙ ሃይልና አሳቤ መሸጋገሯ መሆኑን ያስረዳሉ።

በቀደሙት ዘመናት በአሜሪካ ብቻ ይዘወር የነበረው ዓለም አቀፍ ሁኔታ አሁን ላይ የቻይናንና ራሽያን ተወዳዳሪነት ማቀፉን ገልጸዋል።

ቻይና የምትከተለው በወዳጃነትና ትብብር ላይ የተመረኮዘ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የብዙዎችን ትኩረት አግኝቶ መቀጠሉን ዶክተር ተሾመ አብራርተዋል።

''ቻይና የአገራትን ሉዓላዊነት አክብራ፤ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ በተግባር የምታሳይ አገር ናት'' ያሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ የቻይና አካሄድ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ አገራት መልካም እድል ይዞ የመጣ ነው ይላሉ።

ቻይና ለመጀመር ያሰበችው 'ግሪን ሌን' የገበያ እድልም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራት የግብርና ምርታቸውን ለቻይና በስፋት እንዲያቀርቡ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቻይና የገበያ እድል ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን የግብርና መር ኢኮኖሚ በእጂጉ የሚደግፍና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ አጠቃላይ የቻይና መንግስት ያሰበው የገበያ አማራጭ አፍሪካን በተግባር የመደገፍን ቁርጠኝነት ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

''የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍ በዘመናት ልዩነት ተለዋዋጭነቱ የሚቀጥል በመሆኑ ቁም ነገሩ በውስጥ አቅም ጣንካራ አኮኖሚ መገንባት ነው'' ብለዋል ዶክተር ተሾመ።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለውና ኢትዮጵያን መለወጥ የሚያስችል ኢኮኖሚ መገንባት የግድ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም