የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል

59

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ካቀደው 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 4 ሚሊዮን ኩንታል ማስገባቱን ገለጸ ።

ተጨማሪ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቻ ደምሴ ተናግረዋል ።

ምርቱ በአዳማ ፣ ሻሸመኔ ፣ባህርዳር ፣ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ በሚገኙ የኮርፖሬሽኑ አምስት ማዕከላት እንደሚሰራጭ ገልጸዋል ።

የስንዴ ስርጭቱ በሚቀጥሉት 15 ቀናት በተጠቀሱት ማዕከላት እንደሚከናወንም ነው የተናገሩት፡፡

የስንዴ ስርጭቱ በአግባቡ መከናወኑንና የሚገባው ቦታ መድረሱን ለመከታተል ኮሚቴ ተዋቅሮ ቁጥጥር እንደሚደረግ ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል ።

11 ቢሊዮን ብር  ወጪ የተደረገበት የስንዴ ምርት በዳቦ ቤቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሬ እና የዱቄት እጥረት ለመቅረፍ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል ።

የስንዴ ምርት ስርጭቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን በመደገፍ በአገሪቷ ላይ የተቃጣውን የኢኮኖሚ ጦርነት ለመመከት እንደሚረዳም ጭምር አብራርተዋል።

ኮርፖሬሽኑ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶችን  የምርት ብዛት ከሚታይባቸው ቦታዎች በማንሳት እጥረት ወዳለበት ቦታ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማድረስ ኮርፖሬሽኑ ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነና በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም