ከጭሮ ከተማ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

68

ጭሮ ፤ ህዳር 22/2014(ኢዜአ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ አስተዳደር ከሚኖሩ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡
የከተማው ነዋሪዎች ለሰራዊቱ ደም በመለገስ ሰራዊቱን በመቀላቀል አጋርነታቸውን እያሳዩ ሲሆን ስንቅ አዘጋጅተው እስከ አፋር ግንባር ድረስ ሄደው መስጠታቸውም ተመላክቷል።

ከንቲባው አቶ መሐመድ ኡመር እንዳሉት፤ ድጋፉ የተሰበሰበው ከነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፤ አባገዳዎች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ  ኮሚቴ በማዋቀር በአንድ ሳምንት ግዜ ውስጥ ነው፡፡

ቀደም ሲልም ከከተማዋ የተወጣጡ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እንደተቀላቀሉ አስታውሰው፤ እሳቸውን ጨምሮ የአስተዳደሩ  አመራሮች ወደ ግንባር በመዝመት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመቆም በቁርጠኝነት መነሳታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ሀገሪቱ  ከተጋረጠባት አደጋ  ለመታደግ ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ፤  ምሁራን ደግሞ  ከምንጊዜውም በላይ የሀገር አንድነት የሚያጠናክር  ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት አንደሚጠበቅባቸው ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ጎሳዬ  በበኩላቸው፤  የከተማው ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎችን በማስተባበር መከላከያ ሰራዊቱ መደገፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የንቅናቄ ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

ነዋሪዎቹ ለሰራዊቱ ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ከማሳየት ባለፈ  ስንቅ አዘጋጅተው እስከ አፋር ግንባር ድረስ ሄደው መስጠታቸውም ተመልክቷል።

በጭሮ ከተማ የከብሽ ኢንተርናሽናል ሎጅ ባለቤት  አቶ ሀብታሙ እናውጋው በሰጡት አስተያየት፤ በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነት መከላከያ ሰራዊቱን ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ  የዜግነት ግዴታቸውን  ለመወጣት 150 ሺህ ብር በግላቸው ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ በቂ ባይሆንም በአካል ሄደው ሰራዊቱን  በመቀላቀል ጭምር ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ባለሀብቱ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም