የቬትናሙ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

91
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 የቬትናሙ ፕሬዚዳንት ትራን ዳይ ኳንግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። ፕሬዝዳንት ኳንግ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ትራን ዳይ ኳንግ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት በፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ነው። ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ስምምነቶችም ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያና ቬትናምን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ያለመ የቢዝነስ ፎረም ይካሄዳል። ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያን ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ ለተመሳሳይ የስራ ጉብኝት ወደ ግብፅ እንደሚያቀኑም ነው የተገለፀው። ኢትዮጵያና ቬትናም በይፋ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 1976 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም