በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ፍሬያማ እንዲሆን ኢህአዴግ ራሱን በማጥራት ለህግ የበላይነትን መስራት አለበት

119
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ፍሬያማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ራሱን በማጥራት የህግ የበላይነትን ማክበር ከአባላቱ መጀመር እንዳለበት ምሁራን ተናገሩ። የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍም አስታውቋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ መገርሳ ሌንጂሶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የህግ የበላይነትን ማክበር ከኢህአዴግ አባላት መጀመር አለበት። ገዢው ፓርቲ የህዝብን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አባላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቀድመው የህዝብ አገልጋይ መሆን አለባቸው ብለዋል። ዶክተር ብርሃኑ እንዳሉት እሳቸውና ሌሎችም በውጭ አገር ሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በተለያየ መልኩ ተሳታፊ በመሆን በአሁኑ ወቅት ዜጎች በነጻነት የመናገር መብታቸው ተከብሯል። ሆኖም ግን በርካታ ለውጦች እየታዩ ባለበት ወቅት ሥርዓት አልበኝነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ብለዋል። ሥርዓት አልበኝነቱን ለመቀነስና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ገዢው ፓርቲ "ራሱን በማጥራት በትክክለኛው መንገድ ሕዝቡን መምራት መቻል አለበት" ብለዋል። በተለይም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሆነው ሥርዓት አልበኝነቱን የሚደገፉና ለውጡ ቀጣይነት እንዳይኖረው የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ለውጡ አይቀሬ መሆኑን ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል ዶክተር ብርሃኑ። እንዲሁም በፓርቲው ውስጥ ሆነው በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙና ሲያፈጽሙ የነበሩ አካላት ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ ህዝቡ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ገዢው ፓርቲ በቀጣይ በሚያካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ ካሉበት ችግሮች ለመላቀቅ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ ቢሰራ የተሻለ መሆኑን ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል። ሌላው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አንዳርጌ ታዬ በበኩላቸው መንግስት አሁን ያገኘውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን ሥርዓት አልበኝነት በአጭር ጊዜ በማስወገድ ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረው በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተለይ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች የተገኘውን ለውጥ ተጠቅመው የህዝቡን ፍላጎት በአግባቡ በማወቅ ለማገልገል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ዶክተር አንዳርጌ ገልጸዋል። ገዢው ፓርቲ ከዚህ በፊት የተሰሩ መጥፎ ነገሮችን ማድበስበስ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከችግሩ ለመውጣት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛና ጠንካራ ሆነው ለሰብዓዊ መብት መከበር ከህዝቡ ጎን ሆነው መሥራት እንደሚገባቸው የገለጹት ዶክተር አንዳርጌ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረው መንግስትና ዜጎች እንዳይተማመኑ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል። የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ገለልተኛና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ በፖሊሲ ጥናትና ትግበራ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚሰራ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም