"ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ሁሌም ማሸነፍን ታውቅበታለች"

66

ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በየዘመኑ ችግር ቢያጋጥማትም በቁርጥ ቀን ልጆቿ ሁሌም ማሸነፍን ታውቅበታለች ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።
የትምህርት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ የደም ልገሳ አድርገዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በየዘመኑ ችግር ቢያጋጥማትም በቁርጥ ቀን ልጆቿ ማሸነፍን ታውቅበታለች ብለዋል።

አሁንም በአሸባሪው ህወሃት የተደቀነባትን የህልውና አደጋ በልጆቿ የጋራ ትግል በአሸናፊነት ትወጣዋለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያዊያን ሰራዊቱን በመቀላቀል፣ በመደገፍና በማገዝ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር ይኖርባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የተቋሙ ሰራተኞች የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች ለሰራዊቱ በአይነትና በገንዘብ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ደም በመለገስ አጋርነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ገልጸው ይሄው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከሚኒስቴሩና ከተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በቅርቡ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በደም ልገሳ መርኃ ግብሩ የተሳተፉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች፤ ለሰራዊታችን ደም በመለገሳችን ተደስተናል ብለዋል።

ከደም ልገሳው በተጨማሪ ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍና አገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የቁጥጥር ባለሙያው ዶክተር እንዳለ ጌታቸው፤ ለአሰራዊታችን ደማችን እንዲሁም ድጋፋችንና እገዛችን አይለይም ብለዋል።

የኤጀንሲው የፈተና አስተዳደር የቡድን መሪ አቶ ጥሩነህ ፈለገ ህይወት በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ህልውና ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም