በህልውና ዘመቻው በመረጃና ኮሙኒኬሽን አውደ ግንባር የምሁራን የላቀ ተሳትፎ ያስፈልጋል

58

ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) በህልውና ዘመቻው ምሁራን በመረጃና ኮሙኒኬሽን አውደ ግንባር በመሰለፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም ማስረዳት አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚል ግልጽ አላማ አንግቦ፤ ጠመንጃ አንስቶ ውጊያ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ዳር እስከዳር ተነስተው በመዝመት፣ በመደገፍና በማገዝ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በደጀንነት፣ በዲፕሎማሲ፣ በልማት፣ በስንቅ ዝግጅት፣ በድጋፍ እንዲሁም በመረጃና ኮሙኒኬሽን አውደ ግንባሮች በመሰለፍ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በህልውና ዘመቻው ምሁራን በመረጃና ኮሙኒኬሽን ግንባር በመሰለፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለመላው ዓለም የማስረዳት ግንባር ቀደም ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

የምእራቡ ዓለም የተለያዩ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ ዓለምን ለማሳሳት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ግንባር ምሁራንና የሚዲያ ባለሙያዎች መመከት አለብን ብለዋል።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ወዳጆ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን የህወሃት አሸባሪ ሃይል ለመመከት በመረጥነው ግንባር መሰለፍ አለብን ብለዋል።

በተለይም ምሁራን እና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም ዳያስፖራዎች ከምናደርጋቸው ሌሎች ድጋፍና እገዛዎች በተጨማሪ በመረጃና ኮሙኒኬሽን ግንባር በመሰለፍ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

በዚህ አውደ ግንባር በተለይ ምሁራን ድርብ ሃላፊነት ስላለብን፤ የላቀ ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሲን አባፊጣ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና እንዲታልፍ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ከአፈ ሙዝ ባለፈ ሌሎች የውጊያ አውደ ግንባሮች መከፈታቸውን ጠቅሰው ሁላችንም መካችና አሸናፊ ሆነን መገኘት አለበን ነው ያሉት።

በውጭም ይሁን በአገር ወስጥ የምንገኝ ለአገራችን ህልውና በጋራ እንቁም፤ በየአውደ ግንባሮቹ እንሰለፍ ሲሉም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በውስጥና በውጭ የተቀናጀ ጦርነት የተከፈተባትን ጦርነት ለመመከት የሁላችንም አብሮነትና ትብብር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ደግሞ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከለለው አዲሱ ናቸው።

የውጭ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እያሰራጩት ያለው መረጃ በብዛት ከአውነታው የራቀ መሆኑን ጠቅሰው ትክክለኛውን መረጃ ለመላው ዓለም ማድረስ በተለይም የመሁራንና የሚዲያው ሃላፊነት መሆኑን ጠቅስዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም