በጋሸና ግንባር የወገን ጥምር ጦር ባደረገው ተጋድሎ ጋሸና ከተማን ጨምሮ በአሸባሪው ሃይል የተወረሩ በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል

228

ህዳር 22/2014 (ኢዜአ) በጋሸና ግንባር የወገን ጥምር ጦር ባደረገው ተጋድሎ ጋሸና ከተማን ጨምሮ በአሸባሪው ሃይል የተወረሩ በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አበሰረ።
በሁሉም ግንባሮች ሽንፈት እየተከናነበና እየሸሸ የሚገኘው ጠላት በግንባር ያጣውን ድል ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎችን በመንዛት ለመሸፋፈን እየሞከረ በመሆኑ ህብረሰተሰቡ ራሱን ከሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገለግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ በጋሸና ግንባር ጋሸና፣ አርቢት፣ አቀትና ዳቦ ከተሞች በመከላከያ ሰራዊት፣ አማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ተጋድሎ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

"ወራሪው ቡደን ለወራት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡን በማስገደድ የገነባውን ባለብዙ እርከን የኮንክሪት ምሽግ በተቀናጅ እቅድ፣ የአመራር ጥበብና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተሰብሯል" ብለዋል።

ድሉ ጠላት የዘራፋችውን ንብረቶችና ራሱን ይዞ ለመውጣት የሚያችለውን እድል ሙሉ በሙሉ የዘጋና  ህልሙን ያከሰመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ግንባር በርካታ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን ካባድ መሳሪያዎች በወገን ጦር ተማርከዋል ነው ያሉት፡፡

በወረኢሉ ግንባር ደግሞ የጃማ ደጎሎ፣ ወረኢሉ፣ ገነቴ፣  ፊንጨፍቱ፣ አቀስታ ከተሞች በጀግኖች የመከላከያ  ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ በጥምረት ባደረጉት ተጋድሎ ነጻ ወጥተዋል።

በሸዋ ግንባር ደግሞ መዘዞ፣ ሞላሌ፣ ሸዋሮቢትና ራሳ አካባቢዎች ከወራሪው ቡድን ነጻ ወጥተዋል።

በምስራቅ ግንባር በጀግናው መከላከያ ሰራዊትና አፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ የተቆጣጣራቸው ጭፍራ፣ ካሳጊታ፣ ቡርቃና ሎሎች አካባቢዎችን ከጠላት በማጽዳት የመንግስት መዋቅርን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም ግንባሮች እየተቀጠቀጠ በመፈርጠጥ ላይ ያለው የጠላት ኃይል እንደልማዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማስተጋባት ስለጀመረ ህብረተሰቡ ራሱን ከሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እንዲጠብቅ ጥሪ እቅርበዋል።

ኀብረተሰቡ በደጀንነት ያደረገው ታላቅ ተጋድሎ ለድሉ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ገልፀው፤ ወደፊትም ደጀንነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።

በዚህም "ንጹሃን ተገደሉብኝ፣ መንገድ ተዘጋብኝ፣ ይህ ቦታ ተመታብኝ" እና መሰል ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ ጠይቀዋል።

በሁሉም ግንባሮች እየተመታ የሚሸሸው ሃይል በተስፋ መቁረጥ ዘረፋና ውድመት እንዳይፈጽም በየአካባቢው ያለው ኀብረተሰብ ተደራጅቶ ራሱንና አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ጠላትን እንዲማርክ እና እጅ በማይሰጡት ላይ ደግሞ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም