ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል

124

ህዳር 22/2014 (ኢዜአ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ምሁራን ገለፁ።
በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሊደፍሯት የሞከሩ ጠላቶቿን አይበገሬ ክንዷን በማሳረፍ አንገታቸውን ደፍተው እንዲመለሱ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የተጎናጸፈችው ነጻነት እና ሉዓላዊነት በጀግኖች ልጆቿ በተከፈለ መስዋዕትነት እንጂ በችሮታ አለመሆኑን ደግሞ የአድዋ ድል ህያው ምስክር ነው፡፡

አሁንም አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር የደቀነባት የህልውና አደጋ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት እየተቀለበሰ ነው።

በሽብር ቡድኑና በውጭ ጠላቶች አገሪቷ ላይ የተከፈተውን የጥፋት በትር ለመመከትና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በግንባር ሆነው ጦሩን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ይህን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ኢብሳ አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያን ህልውና ለማጥፋት የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱትን እርምጃ ተገቢና ትክክለኛ ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውሳኔያቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር በመሰለፍ "በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አልደራደርም" ያሉትን ቃል በተግባር ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተከብሮና ፀንቶ የሚኖረው ሁሉም በየተሰማራበት ግንባር አመርቂ ውጤት ሲያስመዘግብ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ አፍሪካን የማዳከም አካል በመሆኑ መላው አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም የሕግ ባለሙያዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም