ዝመት፣ አካባቢህን ጠብቅና መከላከያን ደግፍ በሚለው ጥሪ መሰረት መዲናችንን በንቃት እየጠበቅን ነው- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

89

ህዳር 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዝመት፣ አካባቢህን ጠብቅና መከላከያን ደግፍ በሚለው ጥሪ መሰረት በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ከተማዋን በንቃት እየጠበቁ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ስልጠና የወሰዱ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የራሳቸውን አደረጃጀት በመፍጠር የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ እያስከበሩ መሆኑ ይታወቃል።

ኢዜአ ትናንት እኩለ ሌሊት ገዳማ በአዲስ አባባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ቅኝት የከተማዋ ነዋሪዎች በየሰፈራቸው ተደራጀትው የአካባቢያቸውን ሰላም እያስከበሩ መሆኑን ታዝቧል።

አስተያይታቸውን የሰጡት ነዋሪዎች የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ በጦር ግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ደጀንነታቸውን ከሚያሳዩባቸው አያሌ ተግባራት አንዱ አካባቢያቸውን በንቃት መጠበቅ ነው።

በዚህም የራሳቸውን የቦታና የጊዜ አደረጃጀት በመፍጠር ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ጸጉረ ልውጦችን ሲያገኙም ለፖሊስ እያስረከቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ግንባር ካመሩ በኋላ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተነቃቅቷል፤ አገር በማዳን ዘመቻው ያለው ተሳትፎም ጨምሯል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ በህብረተሰቡ የተቀናጅ አካባቢን የመጠበቅ ስራ ያለምንም የጸጥታ ችግር ክዋኔዋን መቀጠሏን ገልጸው፤ ወደፊትም በንቃት ከተማቸውን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ቢኒያም ረጋሳና ጋሻው ሞላ አካባቢህን ጠብቅ ዝመት መከላከያን ደግፍ የሚለውን እኛ ዘምተን ግንባር ባንገኝም እንኳን አካባቢችንን ነቅተን ከሁሉም ነገር ንጹህና የነቃች ሰፈር እንድትሆን ያሉትን ሰዎች በደንብ በንቃት እየጠበቅን ነው። ብለዋል።

በየወረዳው የሚገኙ አመራሮች ህብረተሰቡን ማደራጀት በቻ ሳይሆን እራሳችውም በፈረቃ ለ24 ሰዓት እየሰሩ መሆኑን፣ በስራ ለይ ያገኘናቸው የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የህብረት ስራ ጽህፍት ቤት ሃላፊ አቶ ብሩክ መንግስቱ ነግረውናል።

የኢትዮጵያን የህልውና አደጋ ለመቀለበስ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ወቅቱ አመራሩ ያለእረፍት የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ሆኖ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም