አሸባሪዎችን ለመደገፍ ሊዘዋወር የነበረ በርካታ ገንዘብ ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

59

ሐረር፤ ህዳር 21 ቀን 2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ ለአሸባሪዎቹ ህውሓትና ሸኔ ድጋፍ ሊውል የነበረ ከፍተኛ የብር መጠን የያዙ የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና ቼኮች ከተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።
የኮሚቴው አባልና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ አዩብ አህመድ በጉዳዩ ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አዩብ እንደገለጹት አሸባሪዎቹን ለመደገፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያ መሰረት በማደረግ ነው።

በተጠርጣሪዎቹ እጅ የተገኙት የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና ቼኮች ሐረር ከተማን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ ባንኮች በስማቸው የወጡ ናቸው።

በሐረር ከሚገኙ ባንኮች  ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ሲሞክሩ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች እጅ የተገኙ ከፍተኛ የብር መጠን የያዙ የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና ቼኮች ለአሸባሪዎቹ ድጋፍ እንዲውሉ የታለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር አሸባሪዎቹን በመደገፍ  የሀገሪቱ ሰላምን ለማወክ የታሰበና የተቀናጀ እኩይ ተግባር መሆኑን አቶ አዩብ አስታውቀዋል።

የኮሚቴው አባልና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ አዩብ እንዳሉት የባንክ ሂሳብ ደብተሮቹና ቼኮቹ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል።

እንዲሁም ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ ሞባይል ስልኮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና  ሰነዶች መያዛቸውን ተናግረዋል።

የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣራ የመምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አባላት ያሉበት ቡድን በክልሉ ተቋቁሞ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም  ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የዕዙ ኮሚቴ፣ ወጣቶችና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ መሆኑን ገልጸው፤ ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም