የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ የህልውና ትግሉ አንዱ የአሸናፊነት ማሳያ ነው

55

አዲስ አበባ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ የህልውና ትግሉ አንዱ የአሸናፊነት ማሳያ መሆኑን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች ማግስት ጀምሮ ከግብፅ ማስፈራሪያና ከሱዳን ቅንነት ማጣት በተጨማሪ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የፓለቲካ ጫና አርፎባታል።

ከእምብርቷ በሚመነጨው የአባይ ወንዝ "ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመሸጋገር" ኢትዮጵያ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከጀመረች በኋላ ያላስተናገደችው ወቀሳ፤ ያልደረሰባት ጫናም የለም።

ሆኖም ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም ነገር ተቋቁመው ከእለት ጉርሳቸው እየቀነሱ፤ ግንባታውን አውን ለማድረግ ቆርጠው በመነሳታቸው ወደ ስኬት እያሸጋገሩት ይገኛሉ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ የህልውና ትግሉ አንዱ የአሸናፊነት ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህም ኢትዮጵያዊያን የቻሉትን ሁሉ በማድረግ የአገራቸው አለኝታ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪና የህልውና ፈተና ውስጥ በሆነችበት አጋጣሚም ቢሆን የግድቡ ግንባታ በስኬት እየተከናወነ መሆኑንም ዶክተር አረጋዊ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ህዳሴ ግድብና መሰል ፕሮጀክቶች እንዲሰናከሉ ከውስጥ ከሃዲዎችና ከውጭ ጠላቶች ጋር እየሰራ ቢሆንም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተመክቶ አላማው እየከሸፈና ሴራው እየመከነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን እየተዋጉ፤ ለግድቡ ግንባታም የድርሻቸውን በማበርከት እየተጉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የግድቡ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀም ከ82 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው በስኬት እየተከናወነ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ተገቢ ባልሆነ መክንያት ከአጎዋ የገበያ አድል በማስወጣት ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው ህዳሴ ግድብና መሰል ፕሮጀክቶች በፍጥነት ከተጠናቀቁ ችግሮቹን የምንቋቋምባቸው የኢኮኖሚ አማራጮች ይሆናሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለምታደርገው ጥረት የግድቡ መገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የጠቀሱት ዶክተር አረጋዊ ሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶችንም እውን በማድረግ የስራ እድል መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን የልማት ስራዎችን በማከናወን እንዲጠናቀቁ ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም