የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እውነቱን የማሳወቅ ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው

116

ሐዋሳ ኅዳር 21/2014 (ኢዜአ) የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እውነቱን በማሳወቅ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የመመከት ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ምሁራን አሳሰቡ።
የመገናኛ ብዙኃን ምሁራን ኢዜአ እንደገለጹት የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በኢትየጵያ ላይ የከፈቱትን የሐሰት ዘመቻ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በእውነትና በተደራጀ መረጃ በመስጠት ማክሸፍ ይጠበቅባቸዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘላለም ገነሞ በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንና በተላላኪዎቻቸው ሀገር ለማፍረስ የሚካሄደውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ የሀገር ውስጥ  መገናኛ ብዙኃን በግንባር ቀደምትነት ልናከሽፈው ይገባል ይላሉ።

በተለይም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚነዙትን የሐሰት መረጃ የሥነ ልቡና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሕዝቡን በማንቃት ሚናችንን መወጣት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገር ለማፍረስ የተወጠነውን ሴራ በዕውቀት፣ በተሟላና ተከታታይነት ባለው መረጃ ለመቀልበስ በተለያዩ ቋንቋዎች እውነታውን በማሳወቅ  ትኩረት መስጠት  እንደሚያስፈልግ አቶ ዘላለም አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ ድርጅቱ ብዝሃነትን አቻችሎና አመጋግቦ ወቅታዊና ትኩስ የሆኑ መረጃዎች በ48 ቋንቋዎች የሀገር ህልውና በማስጠበቅና የጠላቶችን ሴራ የሚያጋልጡ ዘገባዎች በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሆኖም የኢትዮጵያን እውነታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ በማህበራዊና በዲጂታል ሚዲያ ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

''አሁን ያጋጠመን ችግር የአገር ህልውና ነው ''ያሉት አቶ ዘላለም፤ ''አገራችንን ከጥፋት ለመታደግ ሁሉም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተቀናጅተውና ተናበው በመስራት እውነተኛ መረጃዎችን ተከታትለው በማቅረብና ሐሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ምዕራባዊያን ሚዲያዎች ስሟን በማጠልሸት ከዓለም ማህበረሰብ ለማግለል የሚጠቀሟቸውን ሐሰተኛ ዘገባዎችና ለማክሸፍ በድረ ገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ጥቅም ላይ ማዋል ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጿል።

በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ ብርሃኑ በጋሻው በበኩሉ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለው ጫና ከዚህ ቀደም የለመደባቸውን የሀገር የማፍረስ አባዜ መድገም ነው ብሏል።

በተለይ ከጋዜጠኝነት መርህና ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ሀቅን ወደ ጎን በመተው ወገንተኝነት የሚንፀባረቅበት የሐሰት ዘገባዎች ላይ መጠመዳቸው በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግሯል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህንን ያልተገባ አካሄድ በመቃወም እያደረጓቸው ሰላማዊ ሰልፎች የዓለም ማህበረሰብ እውነታውን ለማገንዘብ እንደረዳ እምነቱን ገልጿል።

''በሁሉም ዘርፍ 'የዓለም ቁንጮ' ነን ከሚሉ ሚዲያ በዚህ ልክ የወረደና ሚዛናዊነት የጎደለ ዘገባ ማየት አሳፋሪ ነው'' ያለው ጋዜጠኛ ብርሃኑ፤ ''የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን እውነታ ለሌላው ዓለም ለማሳወቅ የጀመሩት ጥረት ከፍ ማድረግ ይጠይቃል'' ብሏል።

አሁን ላይ እየታየ ያለውን የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና የማያሳድረውን ተፅዕኖ ግልጽ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ በተለያዩ አማራጮች ለማስፋፋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጸው  የሲዳማ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ወንድሙ ጌቱ ነው ።

ማህበረሰቡ በሐሰተኛ ዘገባዎች እንዳይሸበር ከተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  አስታውቋል።

በዚህም ማህበረሰቡ ለመከላከያ ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርግና ሀገር እንዲታደግ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል ።

የኢትዮጵያን ህልውና በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንደማይደፈር ለመላው ዓለም ከማስገንዘብ በተጓዳኝ የህልውናው ዘመቻ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡን በቋሚነት ማንቃት የዕለት ተዕለት ሥራ አድርጎ መስራት ወሳኝነት አለው ብሏል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እየተሰነዘሩብን ያሉ የሐሰት ዘገባዎች መመከት በሚያስችል መልኩ አቅማቸውን አሟጦ መጠቀም እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህርት ሕይወት ዮሐንስ ናቸው።

አሁን ላይ የተከፈተብንን ጦርነትና የደረሰብንን ጉዳት በሚያሳይ መልኩ በተለያዩ ተደራሽ በሚሆኑ ቋንቋዎች በዲጂታልና በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር በመሥራት ዘመቻውን መቀልበስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም