የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ትራንስፖርት ቢሮ ለአገር መከላከያ ሠራዊት 25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

56

ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ትራንስፖርት ቢሮ ለአገር መከላከያ ሠራዊት 25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።
በዛሬው ዕለትም የተቋሙ ሠራተኞች ''ሕይወቱን ለሰጠኝ ደሜን እሰጠዋለሁ'' በሚል መሪ ኃሳብ ለመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርኃ ግብር ለሦስተኛ ዙር አካሂደዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ ተቋሙ ለሕልውና ዘመቻው አስፈላጊውን ድጋፍ በማደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለአብነትም የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሠራዊት በመለገስ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

ለሕልውና ዘመቻው ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ በተደረገው የኃብት ማሰባሰብ መርኃ ግብር 3 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ 12 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ተቋሙ እስከሁንም በድምሩ 25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት  ድገመደረጉን ተናግረዋል።

ደም የለገሱ የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሰራተኞች ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ ግንባር ድረስ በመዝመት አገራቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን ሠራተኞቹ አረጋግጠዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎችን ለመርዳት የአልባሳትና የምግብ ማብሰያ ቁሳቀቁስ ድጋፍ ለማድረግ እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም