ምክር ቤቱ ለተፈናቃዮች ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ለተፈናቃዮች ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረገ
ድሬዳዋ፣ ህዳር 21/2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ለአስተዳደሩ አስረከበ።
ምክር ቤቱ ለአገር ሉዓላዊነትና አንድነት መረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል 50 ኩንታል ሩዝ፣ 250 ካርቶን ቴምር፣ 15 ካርቶን የምግብ ዘይትና አልባሳት ዛሬ ለድሬዳዋ አስተዳደር ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል፡፡
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሼህ መሐመድ አብደላ በርክክብ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት ድጋፍ ከመስጂዶችና ከሀይማኖቱ ተከታዮች የተሰበሰበ ነው፡፡
ተፈናቃዮችን በጊዜያዊነት ከመደገፍ ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለአገር ህልውና፣ ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
"አሸባሪው ህወሃት ለአገር ፣ለወገን፣ ለኃይማኖት ጨምሮ ለማንምና ለምንም ጉዳይ እንደሌለው በሥልጣን ዘመኑ አረጋግጧል" ያሉት ደግሞ ኡስታዝ ነስረዲን አብዱረህማን ዳሞታ ናቸው፡፡
''ኃይማኖት የሚኖረው እንዲሁም ወጥቶ መግባት የሚቻለው አገር ስትኖር በመሆኑ ለአገራችን ህልውና መረጋገጥ ድጋፍ እናደርጋለን'' ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ምክር ቤቱ ለአገር ህልውና መረጋገጥ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያጠናክር ከንቲባው ጠይቀዋል፡፡