ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ ውዴታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው

59

አዲስ አበባ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ክብር መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ ውዴታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው ሲል የአዲስ አበባ ባለሀብቶች ፎረም ገለጸ።

የህልውና ዘመቻው ተቧድነው ሀገራችንን ሊያፈርሱ የመጡ ምእራባውያንን ተባብረን የምናሳፍርበት መሆኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ስትቸገር ልጆቿ በተባበረ ክንድ ከገባችበት አጣብቂኝ እያወጧት፤ አለቀላት ሲባልም እንደ ሻማ ቀልጠው እያሻገሯት በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ዛሬም የገጠማትን ፈተና በድል አድራጊነት እንድትወጣ ልጆቿ ''ከሀገሬ በፊት እኔን'' ብለው ቆርጠው ተነስተዋል።

ለዚህም ነው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በውጭ ሀይሎች እየታገዘ አገር የማፍረስ ሴራውን እውን ለማድረግ  ሲሞክር መላው ኢትዮጵያዊ በቁጣ በዓለም አደባባይ ተሞ የወጣው።

ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ለእናት አገሩ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መቀላቀላቸውም ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው።

በአውደ ውጊያ መሰለፍ ያልቻሉ ደግሞ ስንቅ በማዘጋጀትና አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ ሰራዊቱን በመደገፍ ደጀንነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ባለሀብቶች ፎረም ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በድል እንድትወጣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል።

ፎረሙ የአዲስ አበባ ባለሀብቶችን በማስተባበር ከከተማው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የሀብት ማሰባሰብ ስራ መስራቱን አንስተዋል።

በዚህም ለሰራዊቱ የተሰበሰበውን ድጋፍ ይዘው ግንባር በመገኘት ሰራዊቱን ለማበረታታት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለአገሩ መስዋዕት እየሆነ ያለውን መከላከያ ሰራዊት መደገፍ ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒትሯ ሳይቀር የዘመቱላት ሀገር ነች፤ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን ዓለምን ያስደመመ ክስተት ጭምር ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የቀደሙት መሪዎቿም ለክብሯ ሲሉ ሲዋደቁ የኖሩ ናቸው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ዛሬም ያንን የድል ታሪክ እየደገምን ነው ብለዋል። 

ባለሀብቶችና  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጭምር የዘመቱት ለአገራቸው ክብር ሲሉ መሆኑን ተረድቶ ሁሉም ሊከተላቸው ይገባል።

ኢትዮጵያ የገባችበት የህልውና ትግል የብቻዋ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ጭምር የምትታገል በመሆኑ መላው አፍሪካዊያን በጋራ በመቆም ጠላትን የምናሳፍርበት ጦርነት ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ፎረም ዋና ጸሃፊ  ወይዘሮ ወይንሸት ታረቀኝ በበኩላቸው፣ አገር ባቀረበችው ጥሪ መሰረት እንደ ግለሰብም እንደ ባለሀብቶች ፎረምም ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በቀጣይም በባለሀብቶች በፎረሙ በኩል የተሰበሰበውን ሀብት በመያዝ በቅርቡ ወደ ግንባር እንደሚያቀኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም