ኢትዮጵያ የታሸገ ውሃ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ልትጀምር ነው

107

አዲስ አበባ ህዳር 21/2014(ኢዜአ) የታሸገ ውሃ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማገኘት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የምግብና መጠጥ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የአፍሪካ የውሃ ማማ "ኢትዮጵያ" በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ብትሆንም በመጠቀሙ ሂደት እስካሁን እምብዛም አልተሳካላትም።

ኢትዮጵያ ከዳሎል አስከ ራስ ደጀን ተፈጥሮ ያደላት ታሪካዊ አገር ስትሆን ዓመቱን ሙሉ የፀሃይ ብርሃን የማታጣ ሁሉም ምድሯ ላይ ተገኝቶ መንፈሱን ሊያድስባት የሚመኛት አገር መሆኗን በርካታ ፃሃፍት ይናገራሉ።

የሰው ዘርና የቡና መገኛ፤ የበርካታ እፅዋትና ብርቅዬ እንስሳት መገኛ የጥቁሮች የድል ታሪክ ማህተም ያረፈባት ኢትዮጵያ አሁንም እምቅ ሃብቷ እንዳልተነካ ይነገራል።

ኢትዮጵያ ከምንጭ ተጠልቆ ውሃ የሚጠጣባት፤ በርካታ ጅረቶች የሚፈስሱባት ብትሆንም እስካሁን አልተጠቀመችባቸውም።

አሁን ላይ ግን የታሸገ ውሃ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማገኘት የሚያስችል ዝግጅት መረጉን የምግብና መጠጥ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት  ኢንስቲትዩት ገልፇል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ታደለ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታሸገ ውሃ የሚያመርቱ ድርጅቶች እየተበራከቱ መሆኑን አመልክተዋል።

ከአምራቾቹ መካከል ጥቂቶቹ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ወደ ጎረቤት አገራት ለመላክ የሚሞክሩ እንደነበሩ አስታውስው፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን ህጋዊ በሆነ መልኩ የታሸገ ውሃ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ በዱባይ ገበያ የኢትዮጵያ የታሸጉ የውሃ ምርቶችን ለመጠቀም ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳሳዩና ወደ ጎረቤት አገራትም ከዚህ ዓመት ጀምሮ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት በአግባቡ በመጠቀምና ምርቶቹን ለዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ በማድረግ፤ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን ትሰራለችም ነው ያሉት።

ለዚህም የአመራረት ሂደታቸውን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲያከናውኑ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የታሸገ ውሃ አምራቾች ቁጥር አሁን ላይ 106 መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም