የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- ባለሀብቶች

53

ጎባ፤ ህዳር 21/2014 /ኢዜአ/ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች አስታወቁ።
አስተዳደሩ በከተማዋ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል፡፡

ባለሀብቶችን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልውና ዘመቻው  የሚውል ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑን በምክክር መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊ ባለሀብቶች መካከል አቶ በለጠ ገመቹ እንዳሉት፤ ሀገሪቱን ከአሸባሪው ቡድን ጥፋት ለመታደግ ኢትዮጵያውያን ለህይወታቸው ሳይሳሱ መስዋትነት እየከፈሉ ይገኛሉ።

ሀገርን አስቀድመው እየተዋደቁ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን ማደረግ እንዳለበት አመልክተው፤ እሳቸውም የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ሀገርን ለማዳን ከጠላት ጋር በግንባር እየተፋለሙ ላሉ የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ ማድረግ ሀገርን ለማዳን  ማገዝ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ሌላው ባለሃብት  አቶ ረታ ከበደ ናቸው፡፡

ለዘመቻው ስኬታማነት ከሌሎች የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት በመጀመሪያው ዙር ስንቅ በማዘጋጀት ወደ ግንባር መላካቸውንም አስታውሰው፤  የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

"በመንግስት የሚፈለግብኝን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ እንዲሳካ  እየደገፍኩ እገኛለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ ማህሙድ ከድር ናቸው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው፤ ባለሀብቱ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ሌላም የህብረተሰብ ክፍል ለሀገራዊው ጥሪው  ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት አኩሪ ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የስንቅ ዝግጅት፣ ደም ልገሳና ሌሎች ድጋፎችን በግንባር እየተፋለሙ ለሚገኙ የወገን ሃይሎች መደረጉን አስታውሰዋልል፡፡

አስተዳደሩ በሁለተኛው ዙር ባለሀብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር  ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ለማሰባሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከታቀደው ውስጥ 14 ሚሊዮን በር በከተማዋ በተለያዩ ስራዎች ከተሰማሩ ባለሀብቶች፤ቀሪው በሌላ የህብረተሰብ ከፍል በጥሬ ገንዘብና በስንቅ ዝግጅት የሚሸፈን መሆኑን ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

በአስተዳደሩ የተደራጁ ወጣቶችም አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦችና ከጸጉረ ልውጦች ነቅተው ለመጠበቅ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም አቶ ንጋቱ  መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም