ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር የፊታችን ቅዳሜ በካናዳ ይካሄዳል

64

ህዳር 21/2014/ኢዜአ/  በአሸባሪው ህወሃት ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ -ግብር የፊታችን ቅዳሜ ሕዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ ይካሄዳል።

የኢትዮ-ካናዳውያውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ(ኢክናስ) የቶሮንቶ ቻፕተር አባል ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለሚካኤል ለኢዜአ እንደተናገረው፤ በመርሃ ግብሩ ላይ  በካናዳ የሚኖሩ ሁለት ሺህ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህም 200 ሺህ የካናዳ ዶላር ለማሰባሰብ እቅድ ተይዟል ነው ያለው።

የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ እየተሟገቱ የሚገኙት ካናዳውያኖቹ ጄፍ ፒርስና ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ፣ ሱዳንን ጨምሮ በተለያዩ አረብ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ከዳፎ ሞሐመድ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደተደረገላቸውም ተናግሯል።

የፊታችን ቅዳሜ ሕዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡም ነው ጋዜጠኛ ብርሃኑ የገለጸው።

ጨረታ፣ሽልማት የሚያስገኙ እጣዎችና ሌሎች የገቢ መሰባሳቢያ መርሃ ግብሮች እንደሚካሄዱም አመልክቷል።

በካናዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በመርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ ለወገናቸው አለኝታ እንዲሆኑ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮ-ካናዳውያውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ(ኢክናስ) ለተቸገሩ ወገኖች ገቢ በማሰባሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ድርጅቱ ከቀናት በፊት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ አህመድ መዝመትን ተከትሎ ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 100 ሺህ የካናዳ ዶላር ማሰባሰቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮ-ካናዳዊያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) ከተቋቋመበት ሕዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት 278 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ለወቅታዊ ጥሪና ለልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም