የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የመላ አፍሪካ ችግር ስለሚሆን ሁሉም ከኢትዮጵያ ጎን መቆም አለባቸው

90

ህዳር 21/2014/ኢዜአ/ "የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለአፍሪካ አህጉር የሚተርፍ ችግር ስለሚሆን መላ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን መቆም አለባቸው" ሲል ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ገለጸ።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1937 የተመሰረተው ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን፤ ኢትዮጵያን በተለያየ መልኩ ሲያግዝ የቆየ ድርጅት ነው።

በአሜሪካ ምስረታውን ያደረገው ይህ ድርጅት ኢትዮጵያ በጣሊያን በኩል የተፈጸመባትን ወረራ ኢ-ፍትሓዊነት ለዓለም ማሳወቁ ይታወቃል።

ድርጅቱ እስካሁን ድረስም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን አጣምሮ ኢ- ፍትሓዊ ጫናዎችን እያጋለጠ ይገኛል።

የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ኪፕ ኢዜኪ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የመላ ጥቁር ሕዝቦች የድል አድራጊነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ የተረጋጋች እንድትሆን ጥቁሮች ሁሉ ይሻሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካልተረጋጋች አህጉሩ የተረጋጋ ሊሆን ስለማይችል አፍሪካዊያን በጋራ ሊቆሙ ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።

''ኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር ሆና እንዳትቀጥል በመፈለግ እየተደረገባት ያለውን ጫና እየተቃወምን እንገኛለንም'' ነው ያሉት።

ምንም እንኳን ዓለምን ለመቆጣጠር ቅዠት ውስጥ ያሉ ጥቂቶች ቢኖሩም ዓለም ግን ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም አምናለሁ ብለዋል።

''በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ኢትዮጵያን የሚደግፉ እልፎችን እያየን ነው፤ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ብዙ መሆናቸውን ነው'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረችና ነጻነቷን ያስጠበቀች አገር መሆኑን አስታውሰው አሁንም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ለኢትዮጵያ አንድነት እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ላይ እየተስተዋለ ያለው ጣልቃ ገብነት መላ አህጉሩን ስለሚጎዳ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አምብሮስ አር ኪንግ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን የጥቁሮችን ሉዓላዊነት ስታስጠብቅ የኖረች ታላቅ አገር መሆኗን ገልጸዋል።

የተወሰኑ ምዕራባውያን ኢትዮጵያንና አፍሪካን ለመከፋፈል እየሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ ''እኛም የምንታገለው የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል ነው'' ብለዋል።

ምዕራባውያን በመገናኛ ብዙሓኖቻቸው አማካኝነት አፍሪካን የማዳከም እቅዳቸውን ለማሳካት የዲፕሎማቲክ መቀመጫ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለችግር በማጋለጥ ነው ይላሉ።

ከኢትዮጵያ በመነሳት ሲሰሩ የተቀረው የአህጉሪቷ ክፍል በምዕራባውያን እጅ ለመውደቅ  ጊዜ ስለማይፈጅ መሆኑን ያስረዳሉ።

ሆኖም ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታውን በድል እንደምትወጣ በማሰብ በሁሉም መልኩ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ እየተዘገበ ያለውን የተሳሳተ ዘገባና መረጃ በመመከት ሂደት ሁሉም ከእውነት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን አማራጭም ይሁን በማሕበራዊ ሚዲያ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ገጽታ ማስተጋባት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም