አንድ ብር እስኪቀረኝ የመከላከያ ሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎችን እደግፋለሁ

131

ህዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) “አንድ ብር እስኪቀረኝ ድረስ የአገር መከላከያ ሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎችን እደግፋለሁ” ሲሉ ባለሀብቷ ወይዘሮ ትልቅሰው ገዳሙ ገለጹ።

የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በመቀናጀት ወረራ የፈጸመውን የህወሓት የሽብር ቡድን እየደመሰሱት ይገኛሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ግንባር መዝመት ተከትሎ መላ ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ ጥሪውን ተቀብለዋል።

ባለሀብቷ ወይዘሮ ትልቅሰው ገዳሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ግንባር ተገኝተው ለጸጥታ ሀይሉ የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፤ ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመሆን በተለያዩ ግንባሮች ለጸጥታ ሀይሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ድጋፍ አድርገዋል።

በዛሬው እለትም ሰንጋዎችን ጨምሮ የእለት ደራሽ የሚሆን እንጀራና የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያና አልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

“ሀገር ሰላም ስታጣ ምን ያህል እንደተረበሽን በጥቂት ቀናት በነበረው ክስተት አይተናል፣ ለዚህ የሰላም ዘብ ደግሞ ማንኛውንም ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

በቀጣይም አንድ ብር እስኪቀረኝ ድረስ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለጸጥታ ሀይሉ ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም