በሲዳማ ክልል ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች 105 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተሰበሰበ

47

ህዳር 20/2014(ኢዜአ)በሲዳማ ክልል ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና አሸባሪው ህወሃት ላፈናቀላቸው ወገኖች የሚውል 105 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ተሰበሰበ፡፡

ድጋፉ የተሰበሰበው ከክልሉ ነጋዴዎች፣የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሆን፤ድጋፉን ወደ ሥፍራው የመሸኘት ሥነ-ሥርዓትም ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር፤ ''ለሕይወቱ ሳይሳሳ እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ላደረጉ የክልሉ ነዋሪዎች ታላቅ አክብሮት አለኝ''ብለዋል።

በድጋፉ በጥሬ ገንዘብ 80 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 25 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የእርድ እንስሳት፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ አልባሳት፣ ዘይትና ሌሎችም ቁሶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሀት ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ጦርነት የከፈተብን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የህዝብ ይሁንታ ያገኘውን መንግስት በሀይል በመጣል በሥልጣን ዘመኑ ሲያካሂድ የነበረውን ዝርፊያና ጭቆና ለማስቀጠል፤ይህ ካልተሳካለትም ሀገርን በመበተን ለማዋረድ ነው ብለዋል።

''ይህንን አደጋ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆማችን የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችንን እየመከትን እንገኛለን'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ድጋፍ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስሰበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ''እኔ እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም በማለት በግንባር ተገኝተው በቁርጠኝነት ጦሩን እየመሩ እንደሚገኙ አውስተው፤ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም መሪያችንን ተከትለን ወደ ግንባር መትመም ይጠበቅብናል ''ነው ያሉት።

በግንባር ከሚደረገው ፍልሚያ ባሻገር በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው እንዲሁም በሚዲያ ዘመቻውና በሌሎች መስኮች አንድነታችንን አጠናክረን በመታገል የጥፋት ሴራዎችን ማምከን ይገባናል ብለዋል።

ዘመቻውን ባጠረ ጊዜ በኢትዮጵያ አሸናፊነት በመደምደም ወደቀደመ ሠላማዊ እንቅስቃሴና የልማት ሥራ መመለስ እንደሚቻል ፅኑ እምነት እንዳላቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

እስካሁን ከሲዳማ ክልል በደጀንነት ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር በርካታ ወጣቶችና የልዩ ኃይል አባላት ከሰራዊቱ ጋር መቀላቀላቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም