"የኢትዮጵያ ትግል የአፍሪካዊያን ትግል ነው"

65

ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ትግል የአፍሪካዊያን ትግል ነው" ሲሉ የአፍሪካ መርነት /ፓን አፍሪካኒዝም/ አስተሳሰብ አራማጆች ገለጹ።

ለአፍሪካ ችግሮች መፍትሔ የሚፈልቀው ከራሳችን ከአፍሪካዊያን ነው፤ የአፍሪካዊያንን ችግር ለመፍታት አፍሪካዊያን በቂ ናቸው ብለዋል።

የምዕራባውያን አገራት አፍሪካ ላይ ዘመናዊ የቅኝ ግዛት ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚያደርጉትን ጥረት የሚቃወም ሠልፍ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ዛሬ ተካሄዷል።

ሠላማዊ ሠልፉን ያዘጋጁት የተባበሩት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር በደቡብ አፍሪካ እና የአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ናቸው።

ሠልፉ ፕሪቶሪያ በሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲና የአውሮፓ ሕብረት መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ተካሄዷል።

በሠልፉ ላይ በደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ ግዛቶች የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን፣ ደቡብ አፍሪካዊያንን ጨምሮ በአገሪቷ የሚኖሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎችና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች ታድመዋል።

ምዕራባዊያን አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ መጫን የሚፈልጉትን ዘመናዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የሚቃወሙ መልዕክቶች በሠልፈኞቹ ተላልፈዋል።

በሠልፉ ላይ የተገኙት አፍሪካዊያንና የአፍሪካ መርነት /ፓን አፍሪካኒዝም/) አስተሳሰብ አራማጆች ዛሬ ሠልፉ ላይ የተገኘነው ከኢትዮጵያ ጎን መሆናችንን ለማሳየት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ትግል የአፍሪካዊያን ትግል በመሆኑ አፍሪካዊያን ኢትዮጵያን ተቀላቅለው መታገል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

'አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት ይችላሉ፤ የማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም' ያሉት የኢትዮጵያ ወዳጆች 'ለአፍሪካ ችግሮች መፍትሔ የሚፈልቀው ከራሳችን ከአፍሪካዊያን ነው' ብለዋል።

ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉትን ጫና አንቀበልም፤ ከአፍሪካ ላይ እጃቸውን ያንሱ ብለዋል።

አፍሪካዊያን አንድ ከሆኑ ጠንካራና የበለጸገ አህጉር መገንባት እንደሚችሉና የራሳቸውን መዳረሻ የመወሰን አቅም እንደሚኖራቸው ነው የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሳብ አራማጆቹ የገለጹት።

በፕሪቶሪያ ለሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲና የአውሮፓ ሕብረት መስሪያ ቤት ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫናና በአፍሪካ ላይ የሚያራምዱትን የኒኦ-ኮሎኒያሊዝም አስተሳሰብ እንዲያቆሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ ተሰጥቷል።

በሠልፉ ላይ "ይብቃ" ወይም #Nomore" መልዕክቶች በስፋት መስተጋባታቸውን ኢዜአ ከሠልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከሠላማዊ ሠልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆነው የአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ከ35 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ዳያስፖራዎችን ያቀፈ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም