ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ የባንዳ ስብስቦች የጥፋት ሴራ ሀገራችን አትፈርስም!

90

ደብረ ብርሃን፤ ህዳር19/2014(ኢዜአ) እናትና አባቶቻችን ከጠላት ጠብቀው በማቆየት ያስረከቡን ሀገራችን ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ የባንዳ ስብስቦች የጥፋት ሴራ አትፈርስም! ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ገለጹ።
''ጣይቱ ለነፃነት'' በሚል መሪ ሃሳብ ሴቶች ለህልውና ዘመቻው ያላቸውን ዝግጁነት በደብረ ብርሃን ከተማ የጎዳና ላይ ጉዞ በማድረግ አረጋግጠዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ ኢትዮያ በቀደሙ  ጥበበኛ መሪዎችና ጀግኖች መስዋትነት ተከብራ ከዚህ የደረሰች ደማቅ ታሪክ ያላት ሃገር ናት።

እናትና አባቶቻች  በከፈሉት መስዋዕትነት ጠብቀው  ያቆዩት ሀገር  መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ የባንዳ ስብስብና ታሪካዊ ጠላቶች የጥፋት ሴራ አትፈርስም ብለዋል።

ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሯሯጡ ጠላቶች  ሀገራችንን አሳልፈን እንደማንሰጥ ሊገነዘቡት ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ።

ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት የተዋደቁ ብዙ ሴቶች መኖራቸውን ከታሪክ መዛግብት መረዳት እንደሚቻል አውስተው፤ የአሸባሪው ወረራን ለመመከት ሴቶች መስዋትነት እየከፈሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ቡድኑን በሸዋ ምድር መውጫ ቀዳዳ ለማሳጣት የደብረ ብርሃን ሴቶች ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሀገራቸው ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በአማራ የምሁራን መማክርት ጉባኤ የቦርድ አባል ዶክተር ሀይማኖት እሸቱ እንደገለጹት፤ በአሸባሪው ህወሃት የደረሰብን ግፍና መከራ እንዲያከትም በሸዋ ምድር ይበቃል ልንለው  የግድ ነው።

ንጹሃን ከመጨፍጨፍ ባለፈ ሞሰብ ገልብጦ እንጀራውን በልቶ ምጣድ ሰብሮ እና እንስሳት ገድሎ የሚሄድ ጠላትን ተረባርቦ ለማስቆም  ወጣቶች በተፈጠረው አደረጃጀት ተጠቅመው ከመከላከያ ጎን እንዲሰለፉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሸባሪው  በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ለመቀልበስ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን የገለፁት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሚስጥረ በቀለ ናቸው።

እስካሁን ለህልውና ዘመቻው በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸውና በገንዘባቸው ሲደግፉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤  ትግሉ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ነው ያመለከቱት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር መዝመት እንዳነሳሳቸው በመጥቀስ  ለጥሪያቸው ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸው አስታውቀዋል።

ወይዘሮ እመቤት ግዛው በበኩላቸው፤ እቴጌ ጣይቱና አፄ ምኒልክ በውጭ ወራሪ ሀይል ላይ የፈፀሙትን አሳፍሮ የመመለስ ገድል በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ  ላይም  ለመድገም በግንባር እሰለፋለሁ ብለዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሴቶች ፤ለህልውናችን እንሞታለን!እናቱ ስትታረድ፣ ሚስቱ ስትደፈር፣  ልጁ ስትሰደድ ቁጭ ብሎ የሚያይ የለም! የእትጌ ጣይቱ ልጆች ነን! የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም